በኦሮሚያ ክልል በጉንፋን መሳይ ወረርሽኝ በሽታ የ78 ሰዎች ህይወት አለፈ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ በተቀሰቀሰ ጉንፋን መሳይ ወረርሽኝ በአንድ ቀበሌ ብቻ የ78 ሰዎች ህይወት አልፏል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ በበኩሉ የወረርሽኙን መከሰት አረጋግጦ አፋጣን ምላሽ ለመስጠት እየጣረ መሆኑን አስታውቋል።

ወረርሽኙ ከምዕራብ ወለጋ በተጨማሪ ቄለም ወለጋ ውስጥ መከሰቱንም ዶይቼ ቬለ ከነዋሪዎች አረጋግዐጫለሁ ብሏል፡፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ የሌሊስቱ ሎጲ ቀበሌ ነዋሪ እንደሚሉት በአካባቢው መቋጫ የታጣለት የጸጥታ ችግር ነዋሪውን ለረሃብ እና የወረርሽኝ በሽታ አጋልጦ በርካቶችን ለህልፈት እየዳረገ ነው።

“አሁን እኛ ጋ ከፍተኛ የምግብ እጦት ይስተዋላል፡፡ ይህም መነሻው ድርቅ አጋጥሞን አሊያም በፋጣሪ ቁጣ ሳይሆን ሰው በፈጠረው ግጭት ወጥቶ ማረስ አይደለም ወጥቶ መግባቱ ፈተና ሆኖ በመሆኑ ነው ብሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ምክንያት ጦርነት ከተቀሰቀሰ አምስት ዓመት አልፎታል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት ነዋሪዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ ለከፋ የጤና ችግሮች እና ለረሃብ እንደተጋለጡ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ በበኩሉ ወረርሽኙ እንደተከሰተ ገልጾ ጉዳዩ ዜጎችን ከወረርሽኙ ጉዳት ለመጠበቅ ከሚመለከታቸው የረድኤት ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ኮሌራ እና የወባ ወረርሽኝ በሽታዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ሲሆን በየጊዜው ህይወታቸው የሚያልፉ ዜጎች ቁጥርም እየጨመረ ይገኛል፡፡

የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች ከባድ ውጊያ በሚያካሂዱበት በአማራ ክልል የኮሌራ ወረርሽኝ ተከስቶ የንጹሃን ህይወት በማለፍ ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

የጤና ባለሙያዎች በጦርነቱ ምክንያት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው መስራት አለመቻላቸው ወረርሽኙን መቆጣጠር እንዳልተቻለ የተገለጸ ሲሆን ከሱዳን ተፈናቅለው የመጡ ስደተኞች ሳይቀር ህይወታቸው ማለፉን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ብቻ 24559 ኢትዮጵያዊያን በኮሌራ በሽታ ሲጠቁ ከዚህ ውስጥ 321 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን እንዳጡ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የኮሌራ ወርርሽኝ በ84 ወረዳዎች ላይ አሁንም አልጠፋም የተባለ ሲሆን የተሻለ የጸጥታ ሁኔታ ባለባቸው አካባቢዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከላከያ ክትባት በመሰጠት ላይ ነው ተብሏል፡፡

ይሁንና የሀገሪቱ 60 በመቶ የህዝብ ብዛት የሚኖርባቸው ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ባለው ጦርነት ምክንያት የጤና ተቋማት የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት እንዲያጋጥማቸው አድርጓል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *