የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እየተባባሳ ነው ያለው ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳስጨነቀው ተናግሯል።
የህብረቱ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል የኢትዮጵያ መንግስት አፋጣን እርምጃ መውሰድ አለበት ብለዋል።
ፍትህና ተጠያቂነት የህብረቱና የኢትዮጵያ ግንኙነት ቀስ እያለ ወደ መደበኛነት ለሚመጣው ግንኙነት ሁኔታዎች ናቸውም ሲሉ ሀሳባቸውን በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ገልጸዋል።
ከሰሞኑን በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ የቀረበ ሲሆን፤ ሀገሪቱ ከፍተኛ ክስ ቀርቦባታል።
በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢትዮጵያ መሪማሪ ሪፖርቱን አቅርቧል።
የመርማሪ ቡድኑ ባለሞያ የሆኑት መሀመድ ቻንዴ ኦቶማን ባለፈው ዓመት ለተመድ የሰብዓዊ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሁኔታ ከገለጽን ወዲህ ሰብዓዊ መብት በሀገሪቱ በእጅጉ ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል።
በትግራይ ክልል ቀጥሏል ስላሉት ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያብራሩት ባለሞያው፤ ከትግራይ ባሻገር በአማራ ክልል እየተባባሰ ያለው ሁኔታ ኮሚሽኑን አሳስቦታል ብለዋል።
ባለፈው ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በኋላ፤ በአማራ ንጹሃን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ያለ ፍርድ ግድያና የጅምላ እስር እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
መሀመድ ቻንዴ ኦቶማን እየቀጠለ ያለው የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት በህዳር 2021 የጀመረው ግዙፍ ጥሰት ቀጣይ ነው ሲሉ በአስቸኳይ ታማኝና አካታች የፍትህ፣ የእውነትና የእርቅ ሂደት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የቀረበው ሪፖርት ላይ ምላሽ የሰጠችው ኢትዮጵያ የቀረበባትን ክስ ውድቅ አድርጋለች።
በጀኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳሰር ጸጋአብ ክበበው ኢትዮጵያ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የወሰደችውን የሰላም እርምጃ ኮሚሽኑ ግምት ውስጥ አለማስገባቱ አሳዛኝ ነው ያሉ ሲሆን፤ የምርመራው መንገድ ላይም ጥያቄ አንስተዋል።
ሪፖርቱን “ከደረጃ የወረደና ፖለቲካዊ” ያሉት አምባሳደሩ፤ “የተሳሳተና ሽንገላ” በማለት ውድቅ አድርገውታል።
ቋሚ ተወካይ አምባሰደሩ በአማራ ክልል ስላለው ሁኔታ ኮሚሽኑ አሉታዊና “የማህበራዊ ትስስር ገጽ ወሬ” አቅርቧል ሲሉም ተችተዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የኢትዮጵያ መሪማሪ ቡድን የተመደበለትን የስራ ጊዜ ሲያጠናቅቅ እንዲበተን ጠይቃለች።