ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ግብጽ በሱዳን መረጋጋት ዙሪያ ባዘጋጀችው የጎረቤት ሀገራት የመሪዎች መድረክ ላይ በተገኙበት ወቅት ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በግድቡ ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ መወያየታቸው ሲገለጽ የግድቡ ውሀ አሞላል ዙሪያ ተወያይተው እስከ መስከረም ወር ድረስ ተቋርጦ የነበረውን የሶስትዮሽ ውይይት ለማስጀመር ተስማምተው ነበር፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የግድቡ ተደራዳሪ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ ካይሮ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡
ሁለተኛው የሶስትዮሽ ውይይትም ዛሬ በአዲስ አበባ የተጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የግድቡ ተደራዳሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ዲፕሎማቶች ተሳትፈዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በሁለት ተርባይኖቹ ሀይል ማመንጨት የጀመረው የሕዳሴው ግድብ በተያዘው ዓመት ደግሞ አምስት ተጨማሪ ተርባይኖች ሀይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ የግድቡ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ተናግረዋል፡፡
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታው 91 በመቶ ደርሷል ተብሏል።
ኢትዮጵያዊያን በሚያዋጡት ገንዘብ እና በመንግስት ወጪ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ በ5ሺህ 200 ሜጋ ዋት ሀይል በማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ፕሮጀክት ነው።
የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 350 ሜጋ ዋት ሀይል ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሀይል በማመንጨት ላይ ይገኛል።
ግድቡ እስካሁን ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።