በአማራ ክልል ለ2016 የትምህርት ዘመን 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች እስካሁን አልተመዘገቡም ተባለ
በአማራ ክልል ለ2016 የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብሎ ከተያዘው ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መካከል እስከ ሰኞ መስከረም 07/2016 ድረስ የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን፤ ለ2016 የትምህርት ዘመን ከነሐሴ 23/2015 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የተማሪዎች ምዝገባ እስከ ሰኞ ድረስ የተመዘገቡት ተማሪዎች 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የተማሪዎችን የምዝገባ ጊዜ እስከ ሚቀጥለው ሳምንት ድረስ ነው ያሉት ኃላፊው “በተያዘው ዓመት ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ በእቅድ ተይዞ በክልሉ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔታ አማካኝነት ምዝገባ ያልተካሄደባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅሰውም፤ “የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች መቼ ምዝገባ መካሄድ እንዳለበት እየተወያየን ነው ብለዋል።
እንዲሁም ለ2016 የትምህርት ዘመን ወደ ክልሉ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን የመማሪያ መጽሐፍት ታትመው መግባታቸውን እና ወደ ትምህርት ተቋማት የማስራጨት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የ2016 የትምህርት ዘመን በክልሉ በቀጣይ ሳምንት እንደሚጀመር ገልጸው፤ ሆኖም ይመዘገባሉ ከተባሉት ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች እስካሁን አለመመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
የተጠቀሰው የተማሪዎች ቁጥር ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን፤ የምዝገባ ቀኑ ሊጠናቀቅ ከአራት የማይበልጡ ቀናት ቢቀሩትም እስካሁን የተመዘገቡት ተማሪዎች 37 በመቶ ብቻ ናቸው ተብሏል።
የተማሪዎች በወቅቱ አለመመዝገብ በክልሉ ከተፈጠረው ቀውስ ጋር እንደሚያያዝም ተጠቁሟል።
በአማራ ክልል ካሳለፍነው ሚያዝያ ወር ጀምሮ የጸጥታ ችግር የተከሰተ ሲሆን ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
በክልሉ ኢንተርኔት ከተዘጋም ሁለተኛ ወሩ ላይ ሲሆን በርካታ ቦታዎች ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ከመሆናቸው በተጨማሪ አሁንም በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ኑው።