በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ የታሰሩ ሰዎች ህይወት በተስቦ በሽታ ማለፉ ተረጋገጠ

190 እስረኞች ታመው ህክምና ሲወስዱ ሶስት ሰዎች ደግሞ በጽኑ ህክምና ክትትል ውስጥ መሆነቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ወይም ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳድር ስር ባለ ሲዳሞ አዋሽ የታሰሩ ሰዎችን አስመልክቶ ያደረገውን ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ነሐሴ 24 እንዲሁም በጳጉሜን 2 እና 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በዚህ ማቆያ ማእከል/ቦታ ባደረገው ጉብኝት እንዲሁም፣ በማቆያ ማእከሉ የሚገኙ ሰዎችን እና የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮን ጨምሮ የሚመለከታቸውን የመንግሥት የጸጥታ አካላት በማነጋገር ክትትል አካሂጃለሁ ብሏል።

በተጨማሪም የማቆያ ማእከሉ አስተባባሪዎች እና ጥበቃ ሲያደርጉ የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላትን፣ በቦታው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ የሕክምና ባለሞያዎችን እና ተጨማሪ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኝ የነበረውን የጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ኃላፊዎችን እና ባለሞያዎችን በማነጋገር ስለጉዳዩ አስፈላጊ መረጃና ማስረጃዎች እንዳሰባሰበም አስታውቋል።
 
በማቆያ ማእከሉ የሚገኙት ሰዎች ውሎ እና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎች ሲሆኑ፤ አረጋውያን፣ ሕፃናት፣ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችም ይገኙበታል።

እነዚህ በተለያየ ጊዜ ወደ ማእከሉ እንዲመጡ የተደረጉ ሰዎች ብዛት በየጊዜው ተለዋዋጭ ሲሆን፣ በሺዎች የሚገመቱ ሰዎች በማቆያ ማእከሉ ውስጥ ይገኙ እንደነበርና ኮሚሽኑ ክትትል ያደረገበትን ጊዜ ተከትሎ እና በዚህ ሪፖርት ዝግጅት ወቅት ቁጥሩ ከግማሽ በላይ ቀንሶ በመቶዎች የሚገመቱ ሰዎች መኖራቸውን ተረድቻለሁም ብሏል።

የማቆያ ማእከሉ አስተባባሪዎች ለኮሚሽኑ እንዳስረዱት የጊዜያዊ ማእከሉ ዋነኛ ዓላማ ከጎዳና ላይ እንዲነሱ የተደረጉትን ሰዎች በመልሶ ማቋቋም ፕሮግራም በማገዝ ወደ መጡባቸው አካባቢዎች እንዲመለሱ እና ከጎዳና ላይ ውሎና አዳር እንዲወጡ ማድረግ መሆኑንና በዚሁ መሠረት በተለያየ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ መጡባቸው አካባቢዎች እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በማእከሉ ከሚገኙት ሰዎች ውስጥ 29 በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ የጥበቃ እና የግንባታ ሠራተኞች እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲለቀቁ እንደተደረገ የማእከሉ አስተባባሪዎች ገልጸዋል ተብሏል።

ስፍራው የተሟላ የንጽሕና ቤቶች አለመኖራቸው እንዲሁም ለግል ንጽሕና መጠበቂያ የሚሆን የውሃና የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት፣ የመኝታ አልጋ፣ ፍራሽና አልባሳት አለመኖራቸው፣ ለማደሪያ የተዘጋጀው ቦታ በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን የማያገኝ መሆኑ እና ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ኮሚሽኑ መመልከቱን በሪፖርቱ ገልጿል።

 
በማቆያ ማእከሉ በቅርቡ በተባይ የሚተላለፍ ሕመም መከሰቱን ተከትሎ ለተላላፊ በሽታው የተጋለጡ ሰዎች ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እንዲሰጥ ተደርጓል። የተከሰተው ተላላፊ በሽታ በተባይ (በቅማል) የሚመጣ የተስቦ በሽታ (Relapsing fever) መሆኑን፣ በመጠለያ ጣቢያው ከነበሩ ሰዎች መካከል 190 ሰዎች በሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ያገኙ መሆኑን እና ክትትሉ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ የ3 ሰዎች ሕይወት ያለፈ መሆኑን እና 3 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ሕክምና እያገኙ እንደነበር ከሕክምና ተቋሙ ማወቅ ተችሏል።

ሰዎችን በግዳጅ ወደ አንድ ማቆያ ማእከል/ቦታ ማስገባት ወይም ለኑሮ ከመረጡት ቦታ ወደማይፈልጉበት አካባቢ እንዲሄዱ ማስገደድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያስከትል መሆኑን ኮሚሽኑ አሳስቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *