በአማራ ክልል በአንድ ቀን ብቻ ከ49 በላይ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

በአማራ ክልል ከትናንት በስቲያ ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2015 የመንግሥት የጸጥታ አካላት በወሰዱት እርምጃ እንዲሁም በድሮን ጥቃት ከ49 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን እናት ፓርቲ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ፓርቲው በመግለጫው ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2015 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ ከተማ የመንግሥት ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ 29 ንጹሃን ዜጎች በየመኖሪያ ቤታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ብሏል፡፡

“ከሟቾች ውስጥም ሕጻናት፣ ወጣቶች እና አረጋውያን እንዳሉበት ከመረጃ ምንጮቻችን አረጋግጠናል።” ያለው ፓርቲው  “በተመሳሳይ ነሐሴ 29 ቀን 2015 በምስራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ፣ ሞሰባ ሽሜ አቦ ቀበሌ አዳራሽ ጎጥ ላይ መንግሥት በፈጸመው የድሮን ጥቃት ከ11 በላይ ንጹሐን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል።” ብሏል።

በዚሁ ቀን በምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ አረፋ መድኃኔዓለም ቀበሌ ልዩ ሥሙ ሐሙስ ገበያ በሚባል ቦታም፤ መንግሥት በፈጸመው የድሮን ጥቃት ከዘጠኝ በላይ ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል ሲል አክሏል።

እናት ፓርቲ “በንጹሐን ዜጎች ላይ በተከታታይ ጊዜያት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በጽኑ አወግዛለሁ።” ያለ ሲሆን፤ “ይህ መንግሥት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈጸመ የሚገኘው ሰቅጣጭ እርምጃና ጭፍጨፋ በታሪክም በሕግም ተጠያቂነትን የሚያስከትል ወንጀል እንደመሆኑ በአስቸኳይ መቆም አለበት።” ሲል አሳስቧል።

ፓርቲው አክሎም፤ “በተደጋጋሚ ጊዜያት ለመግለጽ እንደሞከርነው የአገራችን ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግሮች የሚፈቱት በጦርነት ሳይሆን በሰከነ እና በሰለጠነ የሀሳብ ጉርብትናና ውይይት ብቻ ነው።” ብሏል።

“መንግሥት በአማራ ክልል እያከናወነ የሚገኘውን ጦርነት በአስቸኳይ አቁሞ ችግሮች በውይይት ማዕቀፍ ብቻ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጠይቀናል።” ያለው እናት ፓርቲ፤ በእልህና ፉክክር የሚመራ ፖለቲካ አገር አፍራሽ መሆኑንም ጠቅሷል።

ፓርቲው “ሰሚ ቢጠፋም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሐቁን እንዲያውቀውና የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም እውነታውን እንዲረዳ የማድረግ ሥራችንን ኃላፊነት እንዳለበት አካል አጠናክረን እንቀጥላለን።” ሲልም ጠቁሟል።

የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ፣ የአፍሪካ ህብረት እና በርካታ የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በአማራ ክልል በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ እንዲቆም በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

እንዲሁም መንግስት ዜጎችን በማንነታቸው ምክንያት የዘፈቀደ እስሩን እንዲያቆም የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *