በትግራይ ክልል የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት አስደንጋጭ መሆኑ ተገለጸ

በትግራይ ክልል ከ100 ሰዎች ውስጥ 10ሩ የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ አለባቸው ተብሏል፡፡

በትግራይ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭት በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል የተባለ ሲሆን ስርጭቱ በ10 ነጥብ 5 በመቶ መጨመሩን የክልሉ ጤና ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ርእየ ኢሳያስ በሰሜኑ ጦርነት ወቅትም ሆነ ከጦርነቱ በኋላ ልቅ በሆኑ ወሲባዊ ጥቃቶች ምክንያት የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በክልል በሚገኙ 37 የጤና ተቋማት በተደረገ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ፤ እስከ ጦርነቱ ጅማሮ 1 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው የቫይረሱ ስርጭት አሁን ላይ 10 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ከ120 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መድረሱን የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው፣ ከእነዚህ መካከል አምስት በመቶ በሚሆኑት ላይ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደተገኘ ገልጸዋል።

“በተለይም ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች በሆኑ ወጣቶች ላይ ቫይረሱ በከፍተኛ መጠን መገኘቱ ጉዳዩን እጅግ አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ያደርገዋል” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

አክለውም፤ በየዕለቱ ከ20 እስከ 25 የሚሆኑ ሰዎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ ምርመራ እንደሚያደርጉ እና ከእነዚህም ውስጥ ቢያንስ በኹለት ሰዎች ላይ ቫይረሱ እንደሚገኝባቸው ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት ሰዎች በሚፈለገው ልክ ወደ ጤና ተቋማት መጥተው ምርመራ እያደረጉ አይደለም” ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ ይህም ለቫይረሱ ስርጭት ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

“ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረ ምርመራ የሚያሳየው በወራት ውስጥ ውስን ሰዎች በቫይረሱ እንደሚያዙ ሲሆን፤ አሁን ግን በቁጥር በርከት ያሉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያሳይ መረጃ ከጤና ተቋማት እየደረሰን ነው ተብሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *