ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሆነው ተሾሙ
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የትምህርት ሚኒስትሩን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር አድርገው ሾሙ።
ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሹመቱን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲቋቋም በ1294/23 የራስ ገዝ አዋጅ በረቀቀው መሠረት እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው 23ኛው መደበኛ ስብሰባ የዩኒቨርሲቲዎችን የራስ ገዝ ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማጽደቁን ተከትሎ ነው።
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው የመማር ማስተማር እና የምርምር ሥራዎችን በላቀ መልኩ እንዲፈጽሙ እንዲሁም የሰው ሀብት እና የፋይናንስ አስተዳደር ነፃነትን በማረጋገጥ በሀገሪቱ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የላቀ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ ከተሾሙት ቻንስለር በተጨማሪም አዲስ የቦርድ አመራሮች የተሰየሙለት ሲሆን ቦረዱም ዩኒቨርሲቲውን በኃላፊነት ሊመሩ የሚችሉ ፕሬዚዳንት እና ም/ፕሬዚዳንቶችን በቀጣይነት እንደሚሾም ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።