አክስዮን ገዢዎች በ500 ሺ ብር አክስዮን በስድስት አመት ውስጥ ከስድስት ሚልየን ብር በላይ እንደሚያገኙ ተገልጿል።
አሸዋ ቴክኖሎጂ በሰው ሃብት አስተዳደር ፣ በሂሳብ መዝገብ አያያዝ እና የቢዝነስ ክንውኖችን ማቀላጠፊያ ሶፍትዌሮችን በማበልጸግ ወደ ስራ የገባ አገር በቀል ድርጅት ነው።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳንኤል በቀለ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግለሰቦች እና ድርጅቶች አክስዮን ገዝተው ትርፍ የሚጋሩበትን ለሶስት ወራት የሚቆይ የአክስዮን ሽያጭ መጀመሩን ተናግረዋል።
የአንድ አክስዮን ዋጋ 2 ሺህ 500 ብር እየሸጠ ያለው አሸዋ ቴክኖሎጂ ትንሹ አክስዮን 500 ሺህ ብር ሲሆን ትልቁ አክስዮን ደግሞ 100 ሚልየን ብር እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የአክስዮን ገዢዎች የገዙትን አክስዮን መጠን 50 በመቶውን ቅድሚያ መክፈል ይጠበቅባቸዋል የተባለ ሲሆን ቀሪ የአክስዮን ድርሻዎችን ደግሞ ውል በገቡ በአንድ አመት ውስጥ ይከፍላሉ ተብሏል።
አምስት ሰዎች ድረስ በጣምራ አክስዮን መግዛት እንደሚችሉ የተገለፀ ሲሆን አክስዮን የሚገዙ ኢንቨስተሮች አሸዋ ከሚሰራው ስራ ከሚገኘው ትርፍ 50 በመቶውን እንደሚወስዱም ተገልጿል።
የ500 ሺህ ብር አክስዮን የገዙ ደንበኞች በስድስት አመት ውስጥ ከስድስት ሚልየን ብር በላይ ሊያገኙ ይችላሉ ተብሏል።
አሸዋ ቴክኖሎጂ በሁለት መቶ ሚልዮን ብር መነሻ ካፒታል የተመሰረተ ሲሆን መነሻ ካፒታሉን ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ አክስዮን በመሸጥ ላይ ይገኛል።
11 የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ያለው አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን ከ1 ሺህ 500 በላይ ባለ አክስዮኖች ያሉት የቴክኖሎጂ ተቋም ነው።