በ2015 በጀት ዓመት ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 61 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በተለይም አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከማልማት እንዲሁም ነባሮችን ከማደስ እና ከመጠገን አንጻር ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል፡፡
የጮቄ ተራራ እና ወንጪ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻዎች በዓለም ቱሪዝም ድርጅት እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም አስታውሰዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ የኢኮ ቱሪዝም መዳረሻ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን በጥናት የመለየት እና መረጃ የማሰባሰብ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡
በበጀት ዓመቱም በርካታ ቁጥር ካላቸው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች 61 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ነው አቶ አለማየሁ የተናገሩት፡፡
የቱሪዝም ገቢው የሚሰበሰበው በሚኒስቴሩ ወይም በክልል ቢሮዎች ሳይሆን በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሚገኙ አካላት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በቀጣይም ዘርፉን ይበልጥ ለማነቃቃት በቱሪዝም ልማት፣ በገበያ ልማት፣ በአገልግሎት ልሕቀት እና ተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ፋና ዘግቧል፡፡
አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት፣ ነባሮችን የማደስ እና የመጠገኑ ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡