የአፍሪካ ህብረት ከአንድ ወር በፊት መፈንቅለ መንግስት ያደረገችው ኒጀርን ከአባልነት አግዷል።
በጀነራል ቲያኒ የሚመራው የኒጀር ጦር በምርጫ ስልጣን በያዙት የኒጀር ፕሬዝዳንት ባዙም ላይ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ተቆጣጥሯል።
ይህን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ኒጀርን ከአባልነት ላልተወሰነ ጊዜ ከስልጣን ማንሳቱን አስታውቋል።
የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች በምርጫ ስልጣን የያዙትን ፕሬዚዳንት መሃመድ ባዙምን ከእስር እንዲፈቱ እና ወደ ቤታቸው እንዲመልሱም ህብረቱ ጥሪ አቅርቧል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት የምዕራብ አፍሪካ ህብረት (ኢኮዋስ) ለወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ተጠባባቂ ሃይል ለማንቀሳቀስ ያሳለፈውን ውሳኔ መመልከቱንም ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እንደዚህ አይነት ሃይል ማሰማራት ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የደህንነት አንድምታ እንዲገመግም ጠይቋል።
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ዲሞክራሲን ወደነበረበት ለመመለስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ካልተሳካ ወታደሮቹን ወደ ኒጀር ለመላክ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የአፍሪካ ህብረት ሁሉም አባል ሀገራቱ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኒጀርን ወታደራዊ ኃይል ህጋዊ ሊያደርግ ከሚችል ማንኛውም እርምጃ እንዲቆጠቡ ጠይቋል፡፡
ከአፍሪካ ውጭ የትኛውም ተዋናይም ሆነ ሀገር የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንደማይቀበለውም በአጽንኦት አስታውቋል።
ከዚህ በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የተቆጣጠሩት የማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ ወታደራዊ መሪዎች ለኒጀር ወታደራዊ መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።