እስራኤል የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚከታተል የጦር መሪ ሾመች

ብርጋዴር ጀነራል ሀርል ክንፎ በኢትዮጵያ ያሉ ቤተ እስራኤላዊያንን ጉዳይ እንዲከታተሉ መሾማቸው ተገልጿል።

እንደ ጀሩሳሌም ፖስት ዘገባ ከሆነ የእስራኤል መንግሥት በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላዊያን የሚያነሱትን ቅሬታ የሚከታተልና የመፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርብ ወታደራዊ መሪ መሾሙ ተገልጿል።

ጀነራሉ የእስራኤል አሊያስ እና የውህደት ሚኒስቴር በኩል እንደተሾሙ የተገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያን በተመለከተ የእስራኤልን ወቅታዊ የስደት ፖሊሲ የሚገመግም ቡድን እንዲያዋቅሩም ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ተብሏል።

ከአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ይሁንታ በመጠባበቅ ላይ ያሉት ጀነራሉ የጥናት ቡድኑ በአዲስ አበባ እና በጎንደር ወደ እስራኤል ለማቅናት በሚጠባበቁ ቤተ እስራኤላውያንን መርዳት ዋነኛ ስራቸው እንደሚሆንም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።

ብርጋዴር ጄኔራል ሃርል ከዚህ ቀደም በእስራኤል ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች ላይ ተመድበው ማገልገላቸው ተገልጿል።

ባሳለፍነው ሳምንት ቤተ እስራኤላዊያን እየሩሳሌም ከተማ በመገኘት በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ መንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ጎንደር እና አዲስ አበባ በሚገኙ መጠለያዎች ጣቢያዎች ወደ እስራኤል ለመሄድ ያሰቡ 4 ሺሕ 226 ቤተ እስራኤላውያን እንዳሉ ተገልጿል።

እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት በጎንደር እና ባህርዳር ያሉ ቤተ እስራኤሎችን ከጦርነት ቀጠና በአውሮፕላን ማስወጣቷ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *