የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት የሆነው ኤምፔሳ (M-PESA) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአገልግሎት ፍቃድ ካገኘ ከሦስት ወራት በኋላ ስራ መጀመሩን አስታወውቋል።
ኩባንያው ባለፉት ሦስት ወራት አስፈላጊ የሲስተም ፍተሻዎችን እና የቴክኒክ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጿል።
ኩባንያው ከዚህ በተጨማሪም ከባንኮች ጋር አብሮ ለመስራት የአጋርነት ስምምነቶች ከመፈራረም ጀምሮ ወኪሎችን መመልመሉን እና ማሰልጠኑንም አስታውቋል።
አገልግሎቱን ለማግኘትም የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኞች የሆኑ ሁሉ የኤምፔሳ አገልግሎትን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።
ደንበኞች የአንድሮይድ (Android) እና የአይኦኤስ (IOS) ስልክ ተጠቃሚዎች በሳፋሪኮም መስመራቸው *733# ላይ በመደወል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል።
የኤምፔሳ መተግበሪያ በ5 ቋንቋዎች የተዘጋጀ እና የአንድሮይድ ተጠቃሚዎች ከፕሌይስቶር በማውረድ መጠቀም የሚችሉት ሲሆን፤ የአይኦኤስ (IOS) ተጠቃሚ ደንበኞቻችን ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በአፕስቶር እንደሚያገኙም ተገልጿል።
የሳፋሪኮም ደንበኞች ኤምፔሳን በመጠቀም በአገር ውስጥ ገንዘብ መላክ፣ ከአገር ውስጥና ውጪ ገንዘብ መቀበል፣ ክፍያዎችን መክፈል፣ የአየር ሰዓት መግዛት፣ ወደ ባንክ ሒሳቦቻቸው ገንዘብ ማስገባት ከባንክ ሂሳባቸው ገንዘብ ወደ ኤምፔሳ መላክ እንደሚችሉ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አስታውቋል።
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ወደ ኢትዮጵያ የቴሌሎም ገበያ የገባው።
ከ25 በላይ የኢትዮጵያ ከተሞች የቴሌሎም አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የደንበኞቹ ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንደደረሱለትም አስታውቋል።
ድርጅቱን ላለፉት ሁለት ዓመታት በስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት አንዋር ሶሳ ከሀላፊነት ተነስተዋል።
ቡአንዋር ሶሳ ምትክም ቤልጂየማዊው የቀድሞ ኤምቲኤን ኡጋንዳ ሀላፊ የነበሩት ዊም ቫንሄልፑት ከመስከረም ጀምሮ ድርጅቱን እንዲመሩ መሾማቸው ተገልጿል።