የጠቅላይ ሚንስትሩ የቀድሞ አማካሪ በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ በሀይል እንደማይፈታ ተናገሩ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት በሚንስትሮች ምክር ቤት የተወሰነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽድቋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የጠቅላይ ሚንስትሩ የደህንነት አማካሪ፣ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር እና የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለምክር ቤቱ አባላት ንግግር አድርገዋል።

አቶ ገዱ ከሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ለየት ባለ መልኩ በአማራ ክልል ስላለው ሁኔታ ባደረጉት ንግግር ከምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ ገጥሟቸው ተቋርጧል።

አቶ ገዶ ንግግራቸው እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ባደረጉት ንግግር ” ብልጽግና መራሹ መንግሥት ራሱ የፖለቲካ ችግር እየፈጠረ ነው” ብለዋል።

“ፓርቲው የፈጠረውን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት የሚሞክረው ከፖለቲካዊ መፍትሄ ይልቅ ወታደራዊ መፍትሄ ሆኗል” የሚሉት አቶ ገዱ ብልጽግና ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ችግሮችን ፈጥሯልም ብለዋል።

አቶ ገዱ በንግግራቸው በአማራ ክልል ያለው ችግር ከሀይል ይልቅ በውይይት የሚፈታ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ይሁንና አቶ ገዱ እያደረጉት ያለው ንግግር በሌሎች የምክር ቤቱ አባላት መቋረጡ ተገልጿል።

የፌደራል መንግስት ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ በማለቱ በአማራ ክልል ተቃውሞ ገጥሞታል።

ይህን ተከትሎም የክልሉ መንግስት የጸጥታ ሁኔታው ከአቅሙ በላይ መሆኑን ገልጾ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ እና ኮምቦልቻ ይደረጉ የነበሩ በረራዎች ተሰርዘዋል።

በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች አሁንም በሀገር መከላከያ እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው የተባለ ሲሆን ተቋርጠው የነበሩ በረራዎች ዳግም ቀጥለዋል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *