ቢኒያም ተክለወይኒ እባላለሁ። ትውልዴ ሽረ ነው። ከጦርነቱ በፊት የፕሪሚየር ሊጉ ተካፋይ የሆነው የስሑል ሽረ ዋና ቡድን ተጨዋች ነበርኩ ። ሊብሮ ነኝ ። አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ዋና አሰልጣኛችን ነበር ። ኳስ እወዳለሁ ። ደጉ ደበበን አደንቃለሁ ። እንደ እርሱ የመሆን ምኞት ነበረኝ ። ተቀራኒ ሆነን ተጫውተናልም::
በኳስ ጨዋታ መከላከልን እወዳለሁ ። አዳነ ሳላ አማኑኤልን ጨምሮ ከብዙ ጎበዝ አጥቂዎች ተፋጥጫለሁ ። ሁሉንም ገትሬ አቁሜያለሁ ። ቡድኔ ጎል እንዳይቆጠርበት በአግባቡ መምራት መከላከል ከስሑል ሽረ ጋር በፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን መሆን የዘወትር ህልሜ ነበር ።
ከሽረ ውጭ ሌላ ክለብ አላውቅም ። በኳስ ጨዋታ መንገዴ የእራሴንም የቤተሰቦቼንም ህይወት መቀየር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመርጦ መጫወት የሌት ተቀን ምኞቴ ነበር ። አንድ ቀን ለዋልያው መጫወት ! ሐገሬን መወከል ! ግን ምን ያደርጋል ? ዕድሌ ነው መሠል በእዛ የጭንቅ ሰዐት የጦርነቱ ወቅት በጥቅምት 10 ሰከልከላ ላይ ጉልበቴን በሞርታር ተመታሁ ። እግሬ ከመቆረጥ በፈጣሪ ችሮታ ተረፈ ።
ተስፋ ቆረጥኩ ። ህልሜ ጨነገፈ ። የኳስ ህይወቴ ጨለመ ። በጦርነት መሃል ሆነን በእዛ ቀውጢ ሰዐት ግንባር ላይ መሣሪያ ታጥቄ እየታገልን ይህ የኳስ ሜዳ ይናፍቀኝ ነበር ። ኳስ ጨዋታን ብቻ አስብ ነበር ። በእግር ኳስ ህይወቴን ለመቀየር መንገዱን ስይዝ ዕድሌ ይህ ሆነ ።
በህይወት እና በሞት መሃል ዕዚህ በረሃ ሆነን ኳስ ስለመጫወት ስሑል ሽረን የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን የማድረግ ደጋፊዎቻችንን ማስደሰት ምኞቴ ነበር ።
ዕነዚህ የምታያቸው ታዳጊዎች እኛ የደረሰብን እንዲገጥማቸው መሆን የለበትም ። ግጭት ጦርነት ያውም በወንድምዓማቾች መሃል ምን ያስፈልጋል ? ምንስ ጠቀመን ? …
ሰላም አብሮነት ፍቅር መተባበር የዋጋ ተመን የለውም ። የጦርነት ትርፉን ሩቅ ሳንሄድ ይኸው በእኔ ማየት ይቻላል ። ይህ ለእኔ ቅስም ሰባሪው የህይወት ዕጣ ፈንታዬ ቢሆንም እነዛ ህፃናት የእኛ ታናናሽ ታዳጊዎች ከኳስ ሜዳ ወደ ጦር ሜዳ እንዲሄዱ መፍቀድ የለብንም ። በማያውቁት እሳት ሲለበለቡ ማየት ምክነት ነው ። ይልቅስ ኳስ ብንገዛላቸው ጫማ መጫወቻያ ሜዳ ብናመቻችላቸው የነገ የሐገር ወገን ኩራት ይሆናሉ።
ብቻ ፈጣሪ ይቅር ይበለን ።
[ ከጦርነቱ በፊት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተካፋይ የነበረው የስሑል ሽረው ሊብሮ ቢኒያም ተክለወይኒ ይቀጥላል ።]
እኔ ከሞርታር አደጋ እግሬ በተዓምር ከመቆረጥ ነው የተረፈው ! ይህ እግሬ ጉልበቴ እግዚአብሔር ብሎ ከዳነ ዳግም ወደ ሜዳ እመልስ ይሆናል ። እንዳማይሆን ብረዳ እራሱ በፅናት ከፈጣሪ ጋር ኳስ መልሶ ለመጫወት እመኛለሁ ። ዕንደገና ለክለቤ ለስሑል ሽረ መጫወት ! የሊብሮ ቦታዬን ማስከበር ለደጋፊዎቻችን የደስታ ምንጭ መሆን እፈልጋለሁ …
[ ቢኒያም ተክለወይኒ የስሑል ሽረው ተከላካይ በታለቅ የሀዘን ድባብ በነገሰበት የሽረ ስቴዲየም የእግር ኳስ ሜዳን አሻግሮ እየተመለከተ የህይወት ገጠመኙን አካፈለኝ ። ቀጠለናም በረጅም ተነፈሰ ። ]
ዋይ አይ አንተ አምላኬ እግር ኳስ የህይወት ደስታ ምንጫችን ነበር … ሲል ከታላቅ ፀፀት ጋር አንገቱን ወደ መሬት ደፋ ። የህይወት ዕጣ ፈንታ ገጠመኙን እያማረረ ወደ ውሰጡ እንዳልተረበሸ እያስመሰለ ሊገልፅልኝ ተጣጣረ …
ዕንዲህ ከሆንኩ በኋላ አሰልጣኛችን ዳንኤል ፀሃይ ጋር ከሦስት አመታት በኋላ ዳግም ተገናኘን ። ዳኒ ሲያየኝ አዘነ ። የሚለው እስኪጠፋው ደነገጠ ።
የጦርነት አስከፊው መልክ ቢኒያም እና ጓደኞቹን በተስፋ ከተሞላው የእግር ኳስ የህይወት መንገዳቸው መልሷል ። ስፖርት በትግራይ በዘመን ቀለም ከደመቀ ውጤታማ አሻራው ጋር ዛሬም በፈተናዎች መሃል በየቦታው በፍቅር ይተገበራል ።
ከመቀለ ተነስተን ወደ አዲግራት ከዛም ወደ ሽረ ከተማ ለማቅናት እንደ አናኮንዳ በተጠማዘዘው የብዘት ከተማ ተራሮች መሃል በወልዋሎ ቢጫ ቀለም በደመቀችው ሚላ ራይድ ነጎድን ። ካፒቴን ሚላ እንደ ሜዳ ቴኒስ ዳኛ ግራ ቀኝ እያገላመጠን የብዘት ተራራ ፈተኝ ቁልቁለትን እርሱ በምቾት እየነዳ እኛ በሰቀቀን እየታዘብን ከአዲግራት ሽረ አደረሰን ።
በፅናት ከቆሙት ከእልፍ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካቸው ጋር የትግራይ ክልል ስምጥር ተራሮች መሃል ሰንጥቀን በመንገዳችን ሁሉ ባለፍናቸው አክሱም አደዋ የመሳሰሉ ከተሞች ስፖርት እግር ኳስ በትግራይ በየሜዳው ዕድሜ ፆታ ሳይለይ ይተገበራል ።
ከመጥፎው ጊዜ ማግስት ወጣቶች የትግል ሸበጥ ጫማዎቻቸውን እንደ ታኬታ ተጠቅመው ዳግም ለመቋቋም እየተጉ ባሉት የትግራይ ክልል ክለቦች ለመታቀፍ በኳስ ጨዋታ ይዋደቃሉ ። ስፖርት የሚፈጥረውን ሰፊ መነቃቃት ወደ ቀድሞዎ መሠረቱ ለመመለስ እየጣሩ ያሉ በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴ የተሰማሩ የክልሉ ነዋሪ የሆኑ ስፖርት ወዳድ ወገኖች በቻሉት አቅም በኳስ ፍቅር የወደቁ ለነገ ህልማቸው ባልተመቸ መንገድ ውስጥ እየታተሩ ያሉ ህፃናት ታዳጊዎችን ለማገዝም ይተጋሉ ።
ዘር ሀይማኖት ብሄር ፖለቲካ የማይሻው ስፖርት በትግራይ ከጦርነቱ ማግስት ሰፊ ማህበራዊ ቀውስ በፈተነው ክልል ቅንጦት ቢመስልም ገብቶን ከተጠቀምንበት ግን አሁንም ሀያል አቅም እንዳለው ከነገ የኮኮብነት ተስፋቸው ጋር በየጥጋጥጉ በትግል የሸበጥ ጫማዎቻቸው በባዶ እግር ከሰፊ ማህበራዊ ቀውስ ጋር እግር ኳስን በፍቅር የሚያንከባልሉ የትግራይ ወጣቶችን የህይወት ፈተናን መታደግ ነው ።
ሩቅ ሆኖ በእራስ የምቾት ዛቢያ ናውዞ መደስኮር ሳይሆን በቦታው ደርሶ ችግር መከራ ፈተናዎቻቸውን ማየት የሁሉ ስፖርት ቤተሰብ ሃላፊነት ነው ። ያኔ ስፖርት ድንብር ተሻጋሪ ዓለምን ያስተሳሰረ ተፅእኖ ፈጣሪ ! የተጣሉትን ያስታረቀ ! የጦፈ ጦርነት ያስቆመ ! ማህበራዊ ትስስርን ከፍ ያደረገ የሰላም መሣሪያ ስለመሆኑ ፅንፍ ካወጣ ግልብ ጥላቻ ርቆ መረዳት ይቻል ይሆናል ።
በትግራይ ክልል በፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ሊግ ብሄራዊ ሊግ የሚገኙ ክለቦችን ከጦርነት ማግስት ከመፍረስ መታደግ ስፖርታዊ መዋቅሩን ጠብቆ የመጋዝ ጥረትን በመደገፍ ከበጎው ስፖርታዊ ዓለማ ዘመቻ ጋር መሰለፍ የእነርሱ ባልሆነ ጥፋት በህይወት ዕጣ ፈንታ አጋጣሚ እንደ ስሑል ሽረው ተከላካይ ቢኒያም ተክለወይኒ ከእግር ኳስ ሜዳ ወደ ጦር ሜዳ ያቀኑ እልፍ በስፖርት ፍቅር የወደቁ በፅናት ከነገ ተስፋቸው ጋር እንደ ለተሰንበት ግደይ ጉዳፍ ፀጋዩ አማኑዔል ገ/ሚካዔል የመሣሠሉት ሆነው እናት ሀገራቸው ኢትዮጲያን ወክለው በአረንጋዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቃችን ደምቀው በዓለም አትሌቲክስ መድረክ በአፍሪካ ዋንጫ የሚያንፀባርቁ በበርካታ የህይወት ውጣ ውረድ የዳበሩ ኮኮቦችን ለማፍራት መንገዱን መጥረግ ለትውልድ የተቀመጠ ብሄራዊ አደራ ነው ።
ከጦርነት ማግስት ሊፈርሱ የታቀረቡ የትግራይ ክልል ክለቦችን ” ኑ በህብረት እንታደግ” በሚል መሪ ቃል በይፋ የተጀመረው በቀጣዮቹ ቀናት በሚዲያ የሚካሄዱ ታላቅ የቴሌቶን Go fund me ማህበራዊ ዘመቻዎችን በመደገፍ ታሪክ እንስራ !
ስፖርት ለሰለም ስፖርት ለፍቅር ስፖርት ለሀገር አንድነት !
በኤፍሬም የማነ