አየር መንገዱ በድረገጹ እንዳስታወቀው ወደ ደሴ፣ ጎንደር፣ባህርዳር እና ላሊበላ የሚያደርገውን በረራ ሰርዣለሁ ብሏል፡፡
የተሰረዙት በረራዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎች እንደሆኑ ገልጾ አየር መንገዱ ወደ ተጠቀሱት አካባቢዎች ለመጓዝ ትኬት የቆረጡ ደንበኞች በረራዎቹ እንደተመለሱ አስተናግዳለሁም ብሏል፡፡
ወደሥፍራው ለመጓዝ ትኬት የቆረጡ መንገደኞች ትኬታቸው ለአንድ ዓመት ያህል የሚያገለግል መሆኑን አውቃችሁ ወደፊት በፈለጋችሁት ቀን ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ መቀየር ትችላላችሁም ብሏል፡፡
ገንዘቡን መመለስ እንፈልጋለን ለሚሉ ደንበኞችም ገንዘብ መመለስ እንደሚቻል ገልጾ በአቅራቢያችሁ ባሉ የአየር መንገዱ ቲኬት ቢሮዎች በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚቻልም አስታውቋል፡፡
ይሁንና አየር መንገዱ በምን በረራዎቹን እንደሰረዘ ያልገለጸ ሲሆን በአማራ ክልል እየተካሄዱ ባለው ጦርነት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መጠየቁ ይታወሳል።
በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በሁለቱ አካላት መካከል ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ አንድ ሳምንት አልፎታል፡፡