በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ለአመታት የተጠራቀመ ብሶት ውጤት እንደሆነ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ጦርነቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ድንገት የተከሰተ ሳይሆን መንግሥት ሃላፊነቱን በተገቢው ሁኔታ ባለመወጣቱ የተከማቹ ሀገራዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች የግለታቸው ጫፍ ላይ ሲደርሱ የተፈጠረ ነው ብሏል።

ፓርቲው በመግለጫው ይህ ለዓመታት የታመቀው ብሶት፣ የመጠቃት ስሜት እና ተስፋ መቁረጥ ገደፉን አልፎ ክልሉን አሁን ላለበት ሁኔታ ዳርጎታል ሲልም አመልክቷል፡፡

የዚህ ቀውስ መሠረታዊ ምክንያት በብልፅግና ውስጥ ያለው የጋራ ራዕይ መጥፋት፣ በየክልሉ እርስ በእርስ በመጓተት ላይ ያሉ ካድሬዎች የሚመሩት የመንግሥት የአስተዳደር ድክመትና በደል እንደኾነ ሊታወቅ ይገባል ሲልም ገልጾታል።

ችግሩን ለማባባስ ፅንፈኛ የዘውጌ ፖለቲካ አስተሳስብን የሚያቀነቅኑ ታጣቂ ኃይሎች በጠራራ ፀሀይ ሰዎችን በመግደል ሽብርና ፍርሃት በመንዛት እንዲሁም ከግል ትርፋቸው ውጪ አንድ ስንዝር አርቀው ማሰብ የማይችሉ ያላቸው ባለሀብቶች የገንዘብ ድጋፍ በማድረጋቸው መሆኑንም ኢዜማ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ፓርቲው በመግለጫው አክሎም እነዚህ ፅንፈኛ እና አርቀው ማሰብ የማይችሉ ያላቸው ባለሃብቶች እነማን እንደሆኑ ግን በግልፅ አልጠቀሰም፡፡

ኢዜማ በሰላማዊ መንገድ የሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ ባልተሰጣቸው ቁጥር መፍትሔዎች ከጉልበት ይመነጫሉ! የሚል አስተሳስብ መሬት እየያዙ እየመጡ መሆኑ እንደሚያሰጋውም አክሏል።

ኢዜማ በክልሉ የተከሰተውን ቀውስ ከማርገብ ጎን ለጎን መዋቅራዊ የሆነ ሀገር አቀፍ የዘላቂ ሰላም መላ እንዲበጅም ጥያቄ አቅርቧል።

ቀውሱ መንግስት ሀላፊነቱን ባለመወጣቱ የመጣ መሆኑን ተገንዝቦ በግልጽ ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ማህበረሰቡን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበትም ይጠይቅ ኢዜማ አሳስቧል፡፡

መንግስት የሚዘውራቸው መገናኛ ብዙሃን የመንግስት ብቻ ሳይሆን የችግሩን ምንጭን ከመሰረቱ በማሳየት በደሎች ተዳፍነው እንዳይቀሩ የመስራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ለመንግሥት ብዙሀን መገናኛዎች ጥሪውን አቅርቧል።

መንግሥት ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን አገናዝቦ ሀገር አቀፍ የዘላቂ ሰላም ፍኖተ-ካርታ በማዘጋጀት መዋቅራዊ እና ሕጋዊ የሰላም ግንባታ በአስቸኳይ ሊተገብር እንደሚገባም ገልጿል፡፡

የፌደራልና የክልል መንግስታት ላለፉት አምሥት ዓመታት የፈጸሟቸውን የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያጠብቡ ያላቸው ተግባራት  በመፈተሽ የሀገሪቱን የፖለቲካ ብዝኃነት የሚያንፀባርቅ የአሳታፊነት መርህን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም አስታውሷል፡፡

መንግስት በሁሉም አካባቢዎች ማኅበረሰቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለማዳመጥ የሚያስችል መድረክ ማመቻቸት ይጠበቅበታል ሲልም ፓርቲው አሳስቧል፡፡

ህዝቡም በበደል ስሜትና በቁጭት ተነሳስቶ አውዳሚ ወደሆነ መንገድ እንዳይጓዝ ደግሞ ደጋግሞ እንዲያስተውል ሲል የጠየቀው ኢዜማ ከአብራኩ የወጣውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሚገባው ክብር ልክ በመረዳት አላስፈላጊ መስዋዕትነቶች እንዳይከፈሉ የሚቻለውን ሁሉ እንዲያደርግ ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል፡፡

በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መጠየቁ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *