ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም በአማራ ክልል ያለው አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ገለጹ

ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም በአማራ ክልል ያለው አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ገለጹ።

የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሉት በአማራ ክልል ያለው አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሁለተኛው ሰፊ የህዝብ ብዛት ያለው የአማራ ክልል ዋና ዋና መተላለፊያ መንገዶች መዘጋት የሰብዓዊ ድጋፍ ስራዎችን ያደናቅፋል ሲሉም ዶክተር ቴድሮስ ተናግረዋል።

በክልሉ የኢንተርኔት መዘጋት የኮሙንኬሽን ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገውም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ግጭቶች በህዝብ ጤና ላይ ወዲያውኑ ጉዳት ያደርሳሉ ያሉት ዶክተር ቴድሮስ ለተራዘመ የጤና እክሎች ይዳርጋሉም ብለዋል።

በመሆኑም በአማራ ክልል የጤና መሰረተ ልማቶች ከጉዳት እንዲጠበቁ፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና አጋሮች ስራቸውን እንደሚቀጥሉም ዶክተር ቴድሮስ አሳስበዋል።

በተያያዘ ዜና በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ “የሰላም ጥረቶች እና ስምምነቶች” በክልሉም መደረግ የሚችልበት ዕድል እንዲፈለግ ዘጠኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጠይቀዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ወቅት የጸጥታ አካላት “ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀሙ”፣ “ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማግለሎች እና ጥቃቶች እንዳይስፋፉ” እንዲሁም “የጅምላ እስሮች” እንዳይፈጸሙም ድርጅቶቹ አሳስበዋል።

ዘጠኙ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *