አሜሪካ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት እንዳሳሰባት ገለጸች

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

ብሊንከን በዚሁ ውቅት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለው ሁኔታ ለቀጠናው ሰላምና ደህንነት ስጋት የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የእርዳታ እህል በፍትሃዊ መንገድ በሚቀርብበት መንገድ ላይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር መክረዋል።

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሉ ልዩነቶችንም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት አሜሪካ ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ ብሊንከን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነግረዋቸዋል ተብሏል።

በአማራ ክልል በሀገር መከላከያ እና ፋኖ መካከል ካሳለፍነው ሚያዝያ ጀምሮ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

ግጭቱ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የክልሉ መንግሥት ጉዳዩ ከአቅሜ በላይ ነው ሲል የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል።

በክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ መባባሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደሴ፣ ጎንደር፣ እና ላሊበላ በረራውን ሰርዟል።

አየር መንገዱ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ባሰራጨው መረጃ ወደ ደሴ፣ ጎንደር፣ እና ላሊበላ የሚያደርገውን በረራ ሰርዣለሁ ብሏል፡፡

የተሰረዙት በረራዎች ዛሬ እና ነገ ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎች እንደሆኑ ገልጾ አየር መንገዱ ወደ ተጠቀሱት አካባቢዎች ለመጓዝ ትኬት የቆረጡ ደንበኞች በረራዎቹ እንደተመለሱ አስተናግዳለሁም ብሏል፡፡

ይሁንና አየር መንገዱ በምን በረራዎቹን እንደሰረዘ ያልገለጸ ሲሆን በአማራ ክልል እየተካሄዱ ባለው ጦርነት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *