የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደሴ፣ ጎንደር፣ እና ላሊበላ በረራውን ሰረዘ

አየር መንገዱ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ባሰራጨው መረጃ ወደ ደሴ፣ ጎንደር፣ እና ላሊበላ የሚያደርገውን በረራ ሰርዣለሁ ብሏል፡፡

የተሰረዙት በረራዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ሊያደርጋቸው የነበሩ በረራዎች እንደሆኑ ገልጾ አየር መንገዱ ወደ ተጠቀሱት አካባቢዎች ለመጓዝ ትኬት የቆረጡ ደንበኞች በረራዎቹ እንደተመለሱ አስተናግዳለሁም ብሏል፡፡

ይሁንና አየር መንገዱ በምን በረራዎቹን እንደሰረዘ ያልገለጸ ሲሆን በአማራ ክልል እየተካሄዱ ባለው ጦርነት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል፡፡

በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መጠየቁ ይታወሳል።

በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በሁለቱ አካላት መካከል ውጊያ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ከነዋሪዎች አረጋግጠናል፡፡

በክልሉ ኢንተርኔት ለምን እንደተቋረጠ ኢትዮ ቴሌኮምም ሆነ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እስካሁን ያሉት ነገር የለም፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *