የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ እና ጎንደር የነበረውን በረራ ሰረዘ

በአማራ ክልል በርካታ ከተሞች በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ከተጀመረ ሳምንታትን ያስቆጠረ ሲሆን ንጹሃን የጉዳት ሰለባ እየሆኑ እንደሆነም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ ተናግረዋል፡፡

አቶ ክርስቲያን አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳድር በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በህዝብ ላይ ተኩስ ከፍቷል ብለዋል፡፡

የግጭቱ መነሻ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ለምን ይፈርሳል በሚል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን የቀድሞ ልዩ ሀይል አባላት እና የፋኖ ታጣቂዎች ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ውጊያ ውስጥ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

የፋኖ ታጣቂዎች ቀስ በቀስ ወረዳዎችን እና ከተሞችን እየተቆጣጠሩ መምጣታቸውን ተከትሎ በታጣቂዎቹ ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮለኔል ጌትነት አዳነ ተናግረዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚያስገቡ መንገዶች ደብረማርቆስ እና ጎንበር ላይ ተዘግተዋል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ከተሞች የሚያደርገውን እለታዊ በረራ መሰረዙን አዲስ ማለዳ ዘግቧል፡፡

ከትናንት ጀምሮም በጎንደር፣ ላሊበላ፣ ጎጃም፣ ሸዋሮቢት እና ሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ በመካሄድ ላይ እንደሆነ የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ደመቀ አክለውም አለመግባባቱን በውይይት እና በድርድር መፍታት እንደሚቻል የአገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶችም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ይልቃል ከፋለ ደግሞ በአማራ ክልል አውዳሚ ግጭት መከሰቱን ተናግረው ክልሉ ለሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ይልቃል አክለውም ነፍጥ ያነሱ ሁሉ የጦር መሳሪያቸውን በማስቀመጥ ወደ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ህዝቡ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የጀመረውን ህግ የማስከበር ስራ እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *