የሩሲያ ምርት የሆነው ላዳ መኪና በኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተመራጭ ነበሩ።
ለዓመታት ገበያውን ተቆጣጥረውት የቆዩት የሩሲያ ላዳ መኪኖች ቀስ በቀስ ከዓለም እና አፍሪካ ገበያዎች እየጠፉ መጥተዋል።
ኩባንያው ምርቶቹን ወደ አፍሪካ ገበያዎች ማቅረብ ያቆመው ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋር በተያያዘ የሩሲያ ተጽዕኖ እየቀነሰ በመምጣቱ እና በገበያ ውድድር ምክንያት እንደሆነ ድርጅቱ ገልጿል።
ሩሲያ ወደ አፍሪካ ገበያዎች ዳግም የመመለስ ፍላጎት ማሳየቷን ተከትሎ ኩባንያው ከወራት በፊት በኢትዮጵያ እና ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ምቹ ሁኔታዎችን ተመልክቶ ተመልሷል።
የኩባንያው ሀላፊዎች በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገውም ነበር።
ይሁንና በፒተርስግበርግ ከየማ እየተካሄደ ባለው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ መካሄዱን ተከትሎ ኩባንያው ዋና ሙቀመጫውን ግብጽ ለማድረግ መወሰኑን ራሺያ ቱዳይ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ የኩባንያው ፕሬዝዳንት ማክሲም ሶኮሎቭ ግብጽ የላዳ ተሽከርካሪ ፋብሪካ እና ምርት ማሰራጫ ማዕከል እንድትሆን ተመርጣለች።
ኩባንያው ከግብጽም በመነሳት ወደመላው አፍሪካ ምርቶቹን በመላክ የአፍሪካ ገበያውን ዳግም የማስቀጠል እቅዱን ይተገብራል ተብሏል።
ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ሌሎች ግንኙነቶችን የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናግረዋል።