ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት 90 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቀደ

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን የ2016 በጀት ዓመት እቅድን ይፋ አድርገዋል።

ስራ አስፈጻሚዋ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በተያዘው በጀት ዓመት ከአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎቶች 90 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል ብለዋል።

ድርጅቱ በ2016 በጀት ዓመት 13 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት የተቋሙን አጠቃላይ ደንበኞች ቁጥር ወደ 92 ሚሊዮን የማድረስ ውጥን መያዙንም ሀላፊዋ አክለዋል።

የቴሌብር ደንበኞችን ወደ 44 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣ የሞባይል ድምጽ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር 75 ሚሊዮን እንዲሁን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ወደ 41 ሚሊዮን ማድረስም የተቋሙ ሌላኛው ግብ ነው ተብሏል።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የቴሌኮም አገልግሎቶች የመጠቀም ምጣኔን ወደ 71 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ወይዘሪት ፍሬህይወት ገልጸዋል።

የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን ከማስፋፋት አንጻር ደግሞ 998 አዲስ የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎችን ለመገንባት ታቅዳል የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 140 ያህሉ በገጠር አካባቢዎች እንደሚገነቡ ተገልጻል።

የ4ጂ ኔትወርክ አገልግሎት ማስፋፊያን በሚመለከት ደግሞ አገልግሎቱን የሚሰጡ ከተሞችን ቁጥር ወደ 440 ከተሞች ለማድረስ መታቀዱን ስራ አስፈጻሚዋ ጠቅሰዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ ግን ድርጅቱ ላቀዳቸው ስራዎች ፈተና ሊሆን ይችላሉ ያሏቸውን ጉዳዮች የጠቀሱ ሲሆን በተለይም የኑሮ ውድነት፣ የጸጥታ እና ደህንነት ችግሮች እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት በተቋሙ ስራዎች ላይ ስጋት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገልጿል።

እንዲሁም ከሳፋሪ ኮም በመቀጠል ሶስተኛው የቴሌኮም ኦፕሬተር ወደ ስራ የሚገባ መሆኑ ሌላኛው የኢትዮ ቴሌኮም ተወዳዳሪ ሊሆን ይችላልም ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌሎም በ2015 በጀት ዓመት 76 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ አግኝቻለሁ ማለቱ ይታወሳል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *