እንደ ወንዶች የዓለም ዋንጫ ሁሉ በየ አራት አመቱ የሚካሄደው የሴቶች እግር ኳስ ዓለም ዋንጫ ነገ ይጀመራል።
አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ በጋራ የሚያስተናገዱት የ2023 የፊፋ ሴቶች ዓለም ዋንጫ አዘጋጆቹ አውስትራልያ እና ኒውዝላንድ የመክፈቻ ውድድር ጨዋታን ያደርጋሉ።
ውድድሩ ከፈረንጆቹ ሀምሌ 20 እስከ ነሀሴ 20 ቀን 2023 ውስጥ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ይካሄዳል ተብሏብ።
ከዚህ በፊት የሴቶች ዓለም ዋንጫ በ24 ብሔራዊ ቡድኖች አማካኝነት ይካሄድ የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ግን ፊፋ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር ወደ 32 ከፍ አድርጎታል።
አፍሪካ በዚህ ውድድር ላይ በአራት ሀገራት የሚወከሉ ሲሆን ናይጀሪያ ፣ ዛምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ተሳታፊ ሀገራት ናቸው።
የናይጀሪያዋ አሲሳት ኦሾላ በውድድሩ ትደምቃለች ተብሎ ከወዲሁ ትኩረት የተሰጣት ተጫዋች ተብላለች።
ኦሾላ በፈረንጆቹ 2014 በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የፊፋ ሴቶች ዓለም ዋንጫ ኮኮብ ግብ አግቢ እና ምርጥ ተጫዋች ተብላ ተመርጣም ነበር።
ለባርሴሎና ሴት እግር ኳስ ክለብ የምትጫወተው ኦሾላ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፉክክር ውስጥ 20 ግቦችን በማስቆጠር ኮኮብ ሆናም አጠናቃለች።
ሌላኛዋ በዘንድሮው የሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይ የምትጠበቀው አፍሪካዊ ተጫዋች ዛምቢያዊቷ ባርባራ ባንዳ ናት።
የ23 ዓመቷ ባርባራ በ2021 በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ሀትሪክ በመስራት የብዙዎችን ትኩረት ስባለች።
የአማካኝ ስፍራ ተጫዋቿ ደቡብ አፍሪካዊቷ ሮፍሎ ጄን በዚሁ የዓለም ዋንጫ ላይ ከሚጠበቁ አፍሪካዊያን ተጫዋቾች መካከል ዋነኛዋ ተብላለች።
ጊዝሌን ቺባክ ሌላኛዋ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከሚጠበቁ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል ስትሆን ሀገሯ ሞሮኮን ለድል እንደምታበቃ ታምኖባታል።
በዘንድሮው የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር ላይ ኮኮብ ተጫዋች እና ኮኮብ ግብ አግቢ ሆና የጨረሰችው ቺባክ በአውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ በተሰናዳው የፊፋ ሴቶች ዓለም ዋንጫ ላይ ለኮኮብ ግብ አግቢነት ከታጩ ተጫዋቾች መካከል ናት።