ለአራት ቀናት የተሰጠው ይህ ስልጠና ከቲንክ ያንግ እና ከአሜሪካው የአቪዬሽን ቦይንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ነው።
ስልጠናው ከ20 ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ ለ60 ተማሪዎች በአዲስ አበባ ተሰጥቷል።
ከሰባት ዓመት በላይ ጀምሮ እድሜ ላላቸው የተሰጠው ይህ ስልጠና ታዳጊዎች ከቴክኖሎጂ ጋር እየተዋወቁ እንዲያድጉ በማሰብ የተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።
ለታዳጊዎቹ የተሰጠው የስልጠና አይነት ዌብሳይት ማበልጸግ፣ ሮቦቲንግ፣ ኮዲንግ እና አርቲፊሻል እንተለጀንስ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ተቋም ቦይንግ የስልጠናው አካል ሲሆን የበጀት ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
በቦይንግ ኩባንያ የመካከለኛው ምስራቅ፣ አፍሪካ እና ተርኪየ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኩልጅት ጋታ ስልጠናው የቦይንግ ማህበራዊ ሀላፊነት አንዱ አካል ነው ብለዋል።
“የኢትዮጵያ መንግሥት ድጅታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የያዘውን እቅድ ለመደገፍ ወደ ኢትዮጵያ መጥተናል ያሉት” ፕሬዝዳንቱ ለቴክኖሎጂ ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎችን ማሰልጠናቸውን አክለዋል።
ቦይንግ ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮም 20 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ በአፍሪካ ካሉ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ኮልጅት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያም ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች የቴክኖሎጂ ስልጠና ከቲንግ ያንግ እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተባብረን ሰጥተናልም ብለዋል ኮልጅት ጋታ።
ስልጠናውን በወሰዱ ታዳጊ ኢትዮጵያዊያን ላይም የቴክኖሎጂ ፍላጎት እና አቅም እንዳላቸው አስተውያለሁ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ በተመሳሳይ ስልጠናዎችን እና ሌሎች ትብብሮችን ማድረጋችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ከለባዊ አካዳሚ እንደመጣች የነገረችን ተማሪ ሔመን ቴዎድሮስ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ናት።
ቲንክያንግ እና የኔታ ኮዲንግ ከቦይንግ ጋር በመተባበር በክረምት ፕሮግራም በተሰጠው የታዳጊዎች ስልጠና ላይ በመሳተፏ ደስተኛ መሆኗን ነግራናለች።
አስትሮ ፊዚስት መሆን እፈልጋለሁ የምትለው ተማሪ ሔመን ይህ ስልጠና መሆን ለምፈልገው ምኞቴ ያግዘኛል ስትልም አክላለች።
ተማሪ ሔመን አክላም የኢትዮጵያን የጥንት ጥበብ ማወቅ የምንችለው ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ስንችል በመሆኑ የእኔም ፍላጎት ኢትዮጵያን የበለጠ ማወቅ እና ማሳወቅ ነውም ብላለች።
የጥንቱን አልያም የአሁኑን ቴክኖሎጂ ብቻ ይዘን መኖር አንችልም የምትለው ተማሪ ሔመን ሁለቱንም ጥበቦች ባንድ ላይ መጠቀም አለብን ለዚያ ደግሞ የዘመነ ቴክኖሎጂ እውቀት ለመያዝ ጥረት ላይ መሆኗን ተናግራለች።