የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ በሰኔ ወር መጨረሻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን አፈናቀላለች ሲል ገልጿል፡፡
ተመድ ኢትዮጵያ የኤርትራ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን፤ የስደተኞችን ሕግን በመጣስ እንዲሁም ክስ ሳይኖርባቸው በዘፈቀደ የማሰር እና የማፈናቀል ተግባሯን በአስቸኳይ እንደታቆም ነው ያሳሰበው።
ድርጅቱ ወደ ሌላ አገር ጥገኝነት ጠይቀው የገቡ ስደተኞችን በጅምላ ማባረርና በዘፈቀደ ማሰር በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ ነው ሲልም ገልጿል፡፡
በዚህም የመንግሥታቱ ድርጅት ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለውን ጥገኝነት ጠያቂዎችን የማሰቃየት፤ በግዳጅ የማፈናቅልና የሰብአዊ መብት ረገጣ አውግዟል።
ኢትዮጵያ በሱዳን ጥገኝነት ጠይቀው ሲኖሩ የነበሩና በጦርነቱ ምክንያት ወደ አገሪቷ የገቡ ኤርትራውያን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ኢ-ሰብአዊ አያያዝ እየተፈጸመች ነው የተባለ ሲሆን፤ ይህም ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን ሙሉ ለሙሉ የጣሰ ድርጊት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ የኤርትራ ስደተኞችን በጅምላ እያፈናቀለች ነው ያለው ድርጅቱ፤ ወላጆች ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ እና ሕጻናት በኢትዮጵያ እንዲቆዩ እየተደረገ ነው ብሏል።
ድርጅቱ አክሎም፤ በግዳጅ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉት ኤርትራውያን ወደ ኤርትራ ከተመለሱ በኋላ የት እንዳሉ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ የገቡትንና የሚገቡትን ስደተኞች የመመዝገብና የሰብአዊ መብቶች አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ኃላፊነት ቢኖርበትም፤ ከመጋቢት 2012 ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ያሉትን አዲስ ስደተኞችን እየመዘገበ አለመሆኑንም ተመድ ጠቅሷል።
ይህም ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የአደጋ ተጋላጭነት ውስጥ እንዲገቡ እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብታቸው እንዳይከበር እንቅፋት ሆኗል ነው የተባለው፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራውያን ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን የገለጸው የመንግሥታቱ ድርጅት፤ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ስደተኞችና ጠገኝነት ጠያቂዎች ያሉበትን ሁኔታ መረጃ እንዲሰጡ እንዲሁም ከዘመዶቻቸውና ከሚፈልጉት ሰው ጋር መገናኘት እንዲችሉ ትብብር እንዲያደርጉ አሳስቧል።