ኢትዮጵያ እና ግብጽ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ችግራቸውን ለመፍታት ተስማሙ

ግብጽ በሱዳን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ያለመ ውይይት የጎረቤት ሀገራት መሪዎችን መጋበዟ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የሱዳን ጎረቤት ሀገራት በመድረኩ ላይ ለመሳተፍ ወደ ካይሮ ያመሩ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከውይይቱ በተጓዳኝ ከፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መወያየታቸው ተገልጿል።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ መወያየታቸው ሲገለጽ የግድቡ ውሀ አሞላል ደግሞ የመሪዎቹ ዋነኛ መወያያ እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያ በግድቡ ውሀ አሞላል ዙሪያ ግብጽን እና ሱዳንን የመጉዳት ፍላጎት የላትም የተባለ ሲሆን በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ተጨማሪ ውይይቶችን ለማድረግ ስለመስማማታቸውም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ፣ ግብጽ እና ሱዳንም በህዳሴው ግድብ ውሀ አሞላል እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያለባቸውን አለመግባባት በአራት ወራት ውስጥ በሚያደርጉት ውይይት ወደ ስምምነት ለመምጣት ተስማምተዋል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የዘንድሮው የህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት ወደ መስከረም ተራዝሟል ማለታቸው ይታወሳል።

እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሀ ሙሌት ወደ መስከረም ያራዘመችው ግብጽ እና ሱዳን ውሀ እስኪደርሳቸው በሚል ነው።

ከ12 ዓመት በፊት ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 85 በመቶ ደርሷል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *