በከተማዋ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ከ4 ሺህ በላይ ትዳር መፍረሱ ተገልጿል
የፈረሰው ትዳር ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ60 በመቶ ጨምሯል ተብሏል
በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት 4 ሺህ 696 ትዳር በፍቺ መጠናቀቁ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የነዋሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሴ እንደገለፁት በ2015 ዓ.ም ከማዕከል እስከ ወረዳ ለ2 ሚሊየን 239 ሺህ 713 ተገልጋዮች አገልግሎት ተሰጥቷል።
ከዚህ ውስጥ 37 ሺህ 397 ጋብቻ እና 4 ሺህ 696 ፍቺ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘንድሮ የተመዘገበው የፍቺ መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፥ የ60 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል።
ለአብነትም በ2014 ዓ.ም 2 ሺህ 937 ፍቺ መመዝገቡን እና በ2015 ዓ.ም ወደ 4 ሺህ 696 ከፍ ማለቱን ፋና ዘግቧል፡፡
አቶ ዮሴፍ ወደ ኤጀንሲ ያልመጡ ፍቺዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገልጸው ይህ አሃዝ በኤጀንሲው የተመዘገበውን ፍቺ ብቻ እንደሚመለከት ነው የተናገሩት።
የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ ይመስገን ሞላ የፍቺ መጨመር አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው ሰዎች ከመስጠት ይልቅ መቀበልን ብቻ ሲያስቡ ግጭት እንደሚከሰት አንስተዋል፡፡
ለፍቺ ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል የገንዘብ እጥረት ፣ የቤተሰብ ጣልቃ ገብነት፣ አለመግባባት፣ የፍላጎት አለመጣጣም (አለመተማመን) ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው።
በተጨማሪም የግላዊነት መብዛት እና የጾታዊነት አክራሪነት ተጠቃሽ መንስኤ ስለመሆናቸው አውስተዋል።
በአብዛኛው የፍቺ መንስኤ ከዝግጅት ማነስ ጋር ሊያያዝ ስለሚችል ስለጋብቻ፣ ቤተሰብ አስተዳደር እንዲሁም ከራስ ይልቅ ለሌላ ሰው መኖርን በንባብና በሌሎች ዘዴዎች ሰዎች እራሳቸውን ቢገነቡ የፍቺ መጠንን ለመቀነስ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።
ፍቺ በቤተሰብ በተለይም በልጆች ላይ ከፍተኛ ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስ እና ጫና እንደሚያሳርፍም ሀላፊው ተናግረዋል ።