በሱዳን ብሑራዊ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መካከል ያለውን ግጭት በመሸሽ ከ60 ሺሕ በላይ ሰዎች በአማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በጋምቤላ ክልሎች በኩል ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ገልጿል።
በአጠቃላይ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት መካከልም ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከ15 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ሱዳናውያን ሲሆኑ፤ ከ13 ሺሕ በላይ ያህሉ ደግሞ የሌላ አገር ዜጎች መሆናቸው ተጠቁሟል።
የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጸ ሲሆን፤ በአገሪቱ ጾታዊ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል።
እንዲሁም ጦርነቱ ከተጀመረበት ባለፈው ሚያዚያ ወር አንስቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን፣ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውና ከግማሽ ሚሊዮን የሚልቁት ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያመላክታል።
የአገሪቱ ወጣቶች ጦሩን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ያቀረቡት የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን፤ የግጭቱ ዋነኛ ተፋላሚ ኃይል ከሆነው ከፈጥኖ ደራሽ ኃይል መሪ ጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ ጋር “መቼም ቢሆን ቁጭ ብዬ አልነጋገርም” ማለታቸው ይታወሳል።
ጄነራል ሀምዳን ዳጋሎ በበኩላቸው፤ በአንድ ሰሞን ከጄነራል አል ቡርሃ ጋር መነጋገር ዋጋ የለውም ብለው የነበረ ሲሆን፣ ቆይተው ደግሞ “ጄኔራል አል ቡርሃ ጦርነቱን ካቆመ የመነጋገር እድል ይኖራል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ሆኖም የተለያዩ አገራት በተለይም አሜሪካና ሳውዲ አረቢያ የሱዳኑ ግጭት ያበቃ ዘነድ ኹለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ለማደራደር ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ፍሬ ሳይፈራ ቀርቶ፣ ግጭቱ ሦስተኛ ወሩን አስቆጥሯል።
እንደ አይኦኤም መረጃ ከሆነ በዚህ ጦርነት ምክንያት 100 ሺህ ዜጎች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሰደዱ የሚጠበቅ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 70 ሺህ ያህሉ ደግሞ በሱዳን ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን አንደሚሆኑ ይገመታል፡፡