የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ህዝብን ይቅርታ ጠየቀች

ቤተ ክርስቲያኗ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጶሳትን እንደምትሾም አስታውቃለች

ቤተክርስቲያኗ ባወጣችው መግለጫ ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በተፈጸመው ሲመት በቤተ ክርስቲያኒቷ ላይ የደረሰውን መከራና ፈተና ለማሳለፍ ሲባል ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን እና ትውፊቷን ባስጠበቀ ሁኔታ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ትረት ስታደርግ መቆየቷን ገልጻለች።

በዚህ መሰረትም የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተደረሰው ስምምነት መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ቀኖናዋን ከስምምነቱ ፤ ስምምነቱን ከቀኖናዋ ጋር በማዛመድ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልል ባሉ ክፍት አህጉረ ስብከት ተመድበው የሚያገለግሉ 9 ኤጲስ ቆጶሳት በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲሾሙ በወሰነው መሠረት ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳትን መልምለው የሚያቀርቡ 7 ብጹዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት መሰየሙን አስታውቃለች።

የተሰየሙት አስመራጭ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ ባወጣው የእጩ ኤጲስ ቆጶሳት መመልመያ መስፈርት መሠረት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጥቆማ ከቀረቡላቸው 75 ቆሞሳት መካከል በትምህርት ዝግጅታቸው ፣ በአሠረ ምንኩስናቸው ፣ በቋንቋ ችሎታቸውና መንፈሳዊ አገልግሎታቸው መስፈርቱን አሟልተው የተገኙትን 18 እጩ ቆሞሳትን ከነሕይወት ታሪካቸው የተሟላ ሪፖርት ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ለቋሚ ሲኖዶሱ መቅረቡ ተገልጿል።

ቋሚ ሲኖዶስም የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በቀረቡት እጩ ቆሞሳት ላይ ምርጫ እንዲደረግ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የስብሰባ ጥሪ መሠረት ከሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተደረገው ባደረገው እጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ወቅታዊ ችግር ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ አበይት ውሳኔዎችን መማሳለፉን ቤተ ክርስቲያኗ በመግለጫዋ አስታውቃለች።

በዚህም መሠረት ዘጠኝ እጩ ኤጲስ ቆጶሳት የተመረጡ ሲሆን በዓለ ሲመታቸው የፊታችን ሀምሌ ዘጠኝ ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚከናወን ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ወቅት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊትና ታሪካዊት ቤተክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን እና ይህን ባለመወጣቷ ይቅርታ ጠይቃለች።

ቤተ ክርስቲያኗ ጦርነቱ እንዲቆም በወቅቱ መግለጫ ባለመስጠቷ ፣ በጦርነቱ መካከል ወደ ትግራይ ክልል መግባትና መውጣት በሚቻልበት ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና መላው ሕዝበ ትግራይን በአካል በቦታው ተገኝታ ባለመጠየቋና ባለማጽናናቷ ይቅርታ መጠየቋን አስታውቃለች።

እንዲሁም ጦርነቱ ቆሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እርቀ ሰላም ከወረደበት ጀምሮ ለደረሰው ጉዳት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ በውሳኔው መሠረት በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሏ ፣ በዚሁም የተነሣ በቤተ ክርስቲያኗና በመላው ሕዝበ ትግራይ መካከል ለተፈጠረው ቅሬታና አለመግባባት ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርታ ጠይቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *