ኢትዮጵያ ለምርጫ ስርዓት ማጠናከሪያ የ30 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኘች

ኢትዮጵያ ዘላቂ ዲሞክራሲን ለማስፈን የሚያስችላትን የምርጫ ስርአት እንድታጠናክር ለማግዝ የሚውል የ30 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የፋናንስ ድጋፍ ስምምነት ፈርማለች፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት መካካል ተፈርሟል፡፡

የበጀት ድጋፉ የምርጫ ቦርድ ተቋማዊ መዋቅርን ለማጠናከር ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ አሳታፊ ፣ተአማኒና ደረጃውን የጠበቀ ምርጫና ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ተቋሙን ማጠናከር፣ ከሲቪክ ተቋማት በጋራ በመሆን በምርጫ ሂደት የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎን ለማሳደግ ይውላል ተብሏል፡፡

እንዲሁም የበጀት ድጋፉ በኢትዮጵያ ነፃ ፍትሀዊ እና ተአማኒ ምርጫ እንዲያከሂድ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንደሚውልም የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ይህ የበጀት ድጋፍ ፕሮጀክት በሚቀጥሉት አራት አመታት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የሀገሪቱን የምርጫ ስርአት በማጠናከር ዘላቂ ዴሞክራሲን ለማስፈን አስተዋጽኦ እንደሚኖረው  ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደምታካሂድ የሚጠበቅ ሲሆን በስልጣን ላይ ያለው ብልጽግና ፓርቲ በርካታ የህዝብ ጥያቄዎችን አልመለሰም በሚል በመተቸት ላይ ይገኛል፡፡

ለአብነትም የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ፣ ሀብት ማፍራት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቶችን አላስከበረም በሚል ይተቻል፡፡

በነዚህ ምክንያቶች ቀጣዩ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ምርጫ አጓጊ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አዳዲስ ፓርቲዎች በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ለመገዳደር በመደራጀት ላይ እንደሆኑ በመናገር ላይ ናቸው፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ የነበሩት ብርቱካን ሚዴቅሳ ባሳለፍነው ሳምንት በጤና ምክንያት የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸው ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *