የደጀን ከተማ ፖሊስ አዛዥ እና ምክትላቸው ተገደሉ

በአማራ ክልል፤ የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ እና ምክትላቸው “በግለሰብ በተፈጸመባቸው ጥቃት” ህይወታቸው አለፈ።

በአማራ ክልል፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን የምትገኘው የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ እና ምክትላቸው በተከፈተባቸው ተኩስ ሲገደሉ ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ለወረዳዋ ፖሊስ አዛዦች ህልፈት ምክንያት የሆነውን ተኩስ ከፍቷል የተባለ ተጠርጣሪን ለመያዝ ፍለጋ እየተከናወነ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

የደጀን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ ጥቃት የተፈጸመባቸው ዛሬ ሰኞ ሰኔ 26፤ 2015 ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ እንደሆነ የወረዳው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ጋሻዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የፖሊስ አዛዦቹ ላይ ተኩስ የተከፈተባቸው፤ በዛሬው ዕለት በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰጠ ያለውን “የስምንተኛ ክፍል ፈተና ደህንነት ለመከታተል ወደ አባይ ሸለቆ ትምህርት ቤት በመኪና እየተጓዙ በነበረበት ወቅት” መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል።

ሁለቱ የፖሊስ አዛዦች “ግልገሌ” የተባለች ቀበሌ ላይ ሲደርሱ “መንገድ ላይ ሲጠብቃቸው ነበር” በተባለ ግለሰብ ተኩስ እንደተከፈተባቸው አቶ ጌታሁን ተናግረዋል።

በዚህ ጥቃት በጥይት የተመቱት የፖሊስ አዛዡ ኢንስፔክተር ዘውዱ እና ምክትላቸው ኢንስፔክተር ወርቁ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ፤ ሹፌራቸው “እግሩ ላይ ተመትቶ” ጉዳት እንደደረሰበት ኃላፊው አክለዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *