ኢትዮጵያ የታዋቂውን ሩሲያዊ ደራሲ ፑሽኪን ሐውልትን ወደ አደባባይ ልትመልስ መሆኗን ገለጸች
የሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በፈረንጆቹ 2002 ላይ ነበር የታዋቂውን የሩሲያዊ የስነ ጽሁፍ ሰው አሌክሳንደር ፑሽኪንን ሀውልት በስጦታ መልኩ ለአዲስ አበባ የሰጠችው።
ይህ ሀውልት ለረጅም ዓመታት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ስር ባለ አንድ አደባባይን የፑሽኪን አደባባይ በሚል የሰየመችው።
በዚህ አደባባይ ላይም የፑሽኪን ሐውልት ተተክሎ የቆየ ቢሆንም የትራፊክ መጨናነቅን ለማስቀረት በሚል አደባባዩ ፈርሷል።
የአሌክሳንደር ፑሽኪን ሀውልትም ወደ ኢትዮጵያ ሙዚየም ግቢ ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጎ ቆይቷል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን ለአልዐይን እንዳሉት የፑሽኪን ሀውልት ወደ አደባባይ ወጥቶ ይተከላል ብለዋል።
“ሀውልቱ የሩሲያን እና ኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ክብር በጠበቀ መንገድ ዳግም ወደተዘጋጀለት አደባባይ ይተከላል” ሲሉም ገልጸዋል አቶ እያሱ።
ከዚህ በተጨማሪም በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት አደባባዮቹ የፈረሱት የካርል ሄንዝ በም፣ የቦብ ማርሌይ እና ሌሎችም ሀውልቶች ተለዋጭ አደባባዮች እየተዘጋጁላቸው እንደሆነም ተገልጿል።
አደባባዮቹ በመፍረሳቸው ምክንያት ከየቦታው ላይ የተነሱት ሐውልቶችም ዳግም ክብራቸውን በጠበቀ መልኩ ይተከላሉ ተብሏል።