ኢትዮጵያ ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ አቀረበች

የኢትዮጵያ መንግስት በፈረንጆቹ 2009 የተመሰተረተውንና ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ በጥምረት የመሰረቱትን “ብሪክስ” (BRICS) የተሰኘ የአገራት ስብስብ ለመቀላቀል ጥያቄ ማቅረቧን አስታውቃለች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሳምንታዊ መግለጫቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያ የብዙ አለማቀፍ ተቋም መስራች መሆኗን ጠቅሰው የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የገለልተኛ አገሮች ንቅናቄና መስራችና ጠንካራ ተሳትፎ ያላት አገር ናት ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሁን እየተለወጠ ባለው የዓለም ሁኔታና የኃይል አሰላላፍ አንጻር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚረዱ ዓለም አቀፍ ተቋማት አባል በመሆን መንግሥት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

“ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ ‘ብሪክስ’ ነው ፣ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ጥያቄ ቀርቧል፣ በጎ ምላሻ ያገኛል ብለን እናስባለን ፣ ክትትልም የምናደርግበትም ይሆናል” ብለዋል ቃል ቀባዩ፡፡

የብሪክስ አገራት ላለፉት አስርት አመታት ለዓለም ኢኮኖሚ እድገት 50 በመቶ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሲሆን ፣ ይህም ቡድኑን በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ልማት ግንባር ቀደም ተጽዕኖ ፈጣሪ እያደረገው መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ለዓብነትም 42 በመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብ የዚህ ስብስብ አባል ሀገራት ዜጎች ሲሆኑ ተጨማሪ አባል ሀገራትን ለመቀበል በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሳውዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ባንግላዲሽ፣ ቱርክ እና ግብጽ ብሪክስን ለመቀላቀል በይፋ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል፡፡

ብሪክስ አመታዊ ጉባኤውን የፊታችን ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት እንደሚያካሂድ ይጠበቃል፡፡

በምዕራባዊያን የተያዘውን የዓለም ስርዓት ለመገዳደር የተቋቋመው ብሪክስ አዲስ የዓለም መገበያያ እና የትብብር መድረክ ይፋ እንደሚያደርግም ይጠበቃል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *