ኢትዮጵያ 59 ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በእስራት ቀጣች
በኦሮሚያ ክልል በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ድንበር በማሻገር የተከሰሱ 161 ደላሎች መካከል 59 ያህሉ ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ቢሮ የህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ መሀመድ ዝያድ እንዳሉት ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በእስራት ተቀጥተዋል፡፡
የህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ድንበር የማሻገር ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩት ግለሰቦች ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ እና ሊቢያ ጠረፎች ካሉ ደላሎች ጋር በቅንጅት ሲሰሩ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ የሆኑ 134 ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ከሀገር በመዉጣታቸዉ ለተለያዩ ጥቃቶች መዳረጋቸዉን ገልጸዋል።
በነዚህ ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ምክንያት ሰለባ ከሖኑት ከ134 ግለሰቦች መካከል 112ቱ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 22 ዓመት መሆናቸው ተጠቁሟል ።
በነዚህ ወጣቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ፣የጉልበት ብዝበዛ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ተብሏል፡፡
ከ161 ህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች መካከል 134 ወንዶች ሲሆኑ 27 የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው።
እነዚህ ደላሎች በ97 የክስ መዝገብ የተከሰሱ ሲሆን 59 የሚሆኑት ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላልፏል።
በዚህም መሰረት ተከሳሾች ከሶስት ዓመት እስከ ሃያ ዓመት እስራት ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን አቶ መሃመድ ዝያድ ተናግረዋል ።
የህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት አዋጅ ተዘጋጅቶ በክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀ ቢሆንም የደላሎችን የወንጀል ቅንጅት መግታት ባለመቻሉም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራበት መሆኑ ተነግሯል።