ኢትዮጵያ ቮልስዋገን የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ አገደች

በቻይና የሚመረተው የቮልስ ዋገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በጊዜያዊነት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ማገዷን አስታውቃለች፡፡

በቻይና ሀገር የሚመረተው የቮልስ ዋገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በጊዜያዊነት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መታገዱን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በቻይና ሀገር ተገጣጥሞ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ የሚገኘው ቮልስ ዋገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሕጋዊ የሆነ ፈቃድ አለመኖሩን የጀርመኑ ኩባንያ በኤንባሲው በኩል በደብዳቤ ለሚኒስቴሩ ማሳወቁ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በቻይና ሀገር የሚመረተው የቮልስ ዋገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ከኩባንያው ሕጋዊ ፈቃድ ያለው መሆኑ እስከሚረጋገጥ ድረስ በጊዜያዊነት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ታግዷል፡፡

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ ክትትል በማድረግና የሕጋዊነት ማረጋገጫ መረጃዎችን የማጥራት ስራም በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሠራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

መንግስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲመረቱ፣ እንዲገጣጠሙና ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለይቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች የአየር ብክለት እያደረሱ ነው በሚል በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በአነስተኛ ግብር ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያበረታታ ህግ በቅርቡ ማጽደቋ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ከ150 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ማቀዷ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *