የትግራይ እና አማራ ክልል አመራሮች ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ተገናኙ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ ባህርዳር ያቀኑ ሲሆን ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ይልቃል ከፋለ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ረዳ እና ልዑካቸው ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ጋር እንዲሁም ከህብረተሰቡ ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በዚህ ውይይት ላይ አቶ ጌታቸው ረዳ ” ዋጋ የማይጠይቅ የሠላም አማራጭ ሳለ በፖለቲከኞች የጠብ ርሃብ ምክንያት በርካታ ጉዳቶች ተከስተዋል ” ብለዋል፡፡

“ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን ልዩነቶቹ ከአማራ እና ትግራይ ሕዝብ በታች ናቸው ” ያሉ ሲሆን ” አሁን የጦርነትን ምዕራፍ ዘግተን የሠላም አማራጮችን የምናይበት ጊዜ ነው ” ሲሉም አክለዋል፡፡

“የሁከት እና ግርግር አጀንዳዎች የሚታያቸው ይኖራሉ፤ ነገር ግን ለሕዝብ ካሰብን እና ከሠራን ከሠላም ውጭ የተሻለ አማራጭ የለንም ” ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ፕሬዜዳንት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው ፤ ” ልዩነቶች ይኖራሉ  ያሉትን ልዩነቶችን ግን በሕግ፣ በሠላም እና በመነጋገር መፍታት የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ነው ብለዋል።

“የአማራ ክልል ሕዝብ እና መንግሥት ለሠላም አማራጮች ዝግጁ ነው ” ያሉት ይልቃል “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ወደ ቀደመው ሁኔታው መመለስ አለበት፣ ትራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴ መጀመር ይኖርበታል” ሲሉም አክለዋ፡፡

ዶ/ር ይልቃል አክለውም “ተከባብረን እና ተደማምጠን ልዩነቶቻችን ለመፍታት መሥራት ይጠበቅብናል” ሲሉ በቀጣይ ሰላማዊ የህዝብ እና የመንግስት ትስስር መፍጠር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

የፖለቲካ አመራሩ የጀመረውን የሠላም ግንኙነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች በተለይ ደግሞ አዋሳኝ አካባቢ ያሉ የሁለቱም ክልል ሕዝቦች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገር መከላከያ የሰሜን እዝ በህወሃት ታጣቂዎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው፡፡

ለሁለት ዓመት በዘለቀው በዚህ ጦርነት በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን አማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልል ደግሞ የጦርነቱ ዋነኛ ሰለባዎች ነበሩ፡፡

ይህ ደም አፋሳሽ ጦርነት ባሳለፍነው ጥቅምት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ሊቆም ችሏል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *