ኢትዮጵያ 50 የኮንስትራክሽን ሰራተኞችን ወደ ጀርመን ልትልክ ነው

በኮንስትራክሽን ሥራ የሚሰማሩ 50 ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ወደ ጀርመን ከማቅናታቸው በፊት አዲስ አበባ ባለው የጀርመን ኢንስቲትዩት ተጨማሪ ስልጠናዎችን በመውሰድ ላይ ናቸው፡፡

በኮንስትራክሽን ሥራ ለመሠማራት የሚያበቃቸውን ሥልጠና ያጠናቀቁ የመጀመሪያው ዙር ባለሙያዎች ወደ ጀርመን እንደሚሄዱ ተገልጿል፡፡

ሥልጠናቸውንና ፈተናቸውን አጠናቀው ጀርመን ከሚገኙ አሠሪዎቻቸው ጋር የሥራ ውል የተፈራረሙት የመጀመሪያዎቹ ተጓዦች በመጪው አንድ ወር ውስጥ  ጉዞ እንደሚያደርጉ ተሰምቷል። 

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በሲቭል ኢንጂነሪንግ፣ በኮንስትራክሽን ማናጅሜንት ቴክኖሎጂ፣ በአርክቴክቸርና መሰል ሙያዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ምሩቃን ወጣቶች ጎኤቴ በመባል በሚታወቀው የጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንዳሉት ሥልጠናው ከሦሥት ዓመት በፊት በቀድሞው ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና የጀርመን ኮንስትራክሽን ማህበራት ፌደሬሽን በጋራ የተጀመረ ነው፡፡

አቶ ንጉሡ ጥላሁን  አዲስ አበባ ባለው ጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ሥልጠናቸውን አጠናቀው፣ የመጨረሻው ምዘና አልፈው እና አስፈላጊውን የሥራ ትዕዛዝ ተቀብለው ወደ ጀርመን ሀገር ለመጓዝ ዝግጀታቸውን ያጠናቀቁትን እንዲሁም በመሠለጠን ላይ የሚገኙትን ምሩቃን በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ግቢ አወያይተዋቸዋል።  

አቶ ኤልያስ አብዶ በኢትዮጵያውያ የጀርመን ኮንስትራክሽ ማህበራት ፌደሬሽን ወኪል ሲሆኑ ሥልጠናውን   የሚከታተሉት ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ከ 50 በላይ የሚሆኑ ሠልጣኞች ሲሆኑ ሥልጠናውን ከጀመሩት መካከል 11 ሰዎች ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የጀርመን ኮንስትራክሽን ፌደሬሽን የሚፈልገውን መስፈርት አሟልተው የመጨረሻውን ፈተና በማለፍ ለጉዞ ዝግጁ የሆኑ ናቸው፡፡

ሁሉንም ሂደቶች ካጠናቀቁት ውስጥ 6 ባለሙያዎች ጀርመን ከሚገኙ አሠሪዎቻቸው ጋር የሥራ ውል ተፈራርመዋል ተብሏል፡፡

የተቀሩትም የሥራ ውል በመጠባበቅ እና ሥልጠናቸውን አጠናቀው የመጨረሻውን ፈተና ለመወቀበል በዝግጅት ላይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ሥልጠናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡

አቶ ንጉሡ ጥላሁን ፤ በጀርመን በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰፊ የሠራተኛ ፍላጎት ቢኖርም የማሠልጠን አቅም ውስን በመሆኑ ሥልጠናውን ለማስፋት ከጀርመን ኮንስትራክሽን ማህበራት ፌደሬሽንና ከጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ጋር በመነጋገር ሥልጠናው በሚሰፋበት ሁኔታ ላይ እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ይህንንም ለማድረግ እንደ አንድ አማራጭ የተወሰደው ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይሰጥ የነበረው የጀርመንኛ ቋንቋ ሥልጠና የተቋረጠ ስለሆነ ትምህርቱ የሚቀጥልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከዩኒቨርስቲው እና ጀርመን ባህልና ቋንቋ ኢንስቲትዩት ጋር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *