ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ከውጭ ለማስገባት ማቀዷን አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዳስታወቀው ለ2016 ዓ/ም ወደ አገር ለማስገባት ለታቀደው 4.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ።
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት የሚያስፈልጋትን ነዳጅ ለማስገባት የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ ” ቪቶል ” የተባለው የባህሬን ኩባንያ በድጋሚ በማሸነፉ የኮንትራት ውል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በ2016 ዓ.ም. ለማስገባት ያቀደውን ሙሉ ለሙሉ ቤንዚን፣ እንዲሁም ከጠቅላላው የነጭ ናፍጣ ግዥ 40 በመቶውን ” ቪቶል ” ኩባንያ እንደሚያስገባ ታውቋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ለ1 ዓመት የሚያስፈልገውን 760 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቤንዚንና 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣ ኩባንያው ያቀርባል ተብላል፡፡
” ቪቶል ” ጨረታውን ያሸነፈው ከሁለት ሌሎች ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሮ እንደሆነ ተነግሯል።
” ቪቶል ” እየተጠናቀቀ ባለው እና ባለፈው የበጀት ዓመት በተመሳሳይ የወጣውን ጨረታ አሸንፎ ነዳጅ ለኢትዮጵያ ሲያቀርብ ነበር።
ለ2016 በጀት ዓመት ያስፈልጋል ተብሎ የታቀደው ነዳጅ ከ2015 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በስምንት በመቶ ብልጫ እንዳለው ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በተናጠል ሲታይ ቤንዚን ስምንት በመቶና ነጭ ናፍጣ አምስት በመቶ ጭማሪ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የዓለም ነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ሲሆን የነዳጅ ጭማሪው በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
ሳውዲ አረቢያ በቀን አንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ምርት እንደምትቀንስ ማሳወቋን ተከትሎ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳይቷል።