በባለስልጣን ጠባቂ ወታደር የተጠለፈችው የባንክ ሰራተኛ እስካሁን ያለችበት አልታወቀም

የዳሽን ባንክ ሐዋሳ ቅርንጫፍ ባለሙያ የሆነችው ፀጋ በላቸው በሐዋሳ ከንቲባ ጠባቂ ኮንስታብል የኋላመብራት ወልደማርያም መጠለፏ ተገልጿል።

የሲዳማ እና ደቡብ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ ይህ መፈጸሙ ብዙዎችን ያስደነገጠ ድርጊት ሆኗል።

ባለሙያዋ በሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ፀጋዬ ቱኬ የግል ጠባቂ ኮንስታብል የኋላመብራት ወ/ማሪያም ተጠልፋ ከተወሰደች ከሳምንት በላይ ሆኗታል።

የተጎጂዋ ቤተሰቦች እንዳሉት የግል ተበዳይ በቤተ ክርስቲያን ደንብ መሰረት የጋብቻ ትምህርት ከወደፊት የትዳር አጋሯ ጋር ተምረው በማጠናቀቅ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ለመጋባት ቀን ቆርጠው የቤት ዕቃዎችን በማሟላት ላይ ነበሩ።

ይሁን እንጂ ጥቃት አድርሷል በሚል በፖሊስ የሚፈለገው ተጠርጣሪ የግል ተበዳይን በተደጋጋሚ ይዝትባት እና ያስፈራራት እንደነበር ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

የግል ተበዳይ ቤተሰቦች ፀጋ ያለችበትን ባለማወቃቸው ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከመሆናቸውም ባለፈ የተበዳይ አባት በጠና ታመው ሕክምና እየተከታተሉ ስለሚገኙ ጉዳዩ ቤተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩንም ጨምረው ገልጸዋል ሲል አዲስ ማለዳ ዘግቧል።

ግንቦት 12 ቀን 2015 የግል ተበዳይ ፀጋ በላቸው፤ ከሥራ ወጥታ ወደ ግል ጉዳይ በምታመራበት ወቅት በተለምዶው  አሮጌው መነሃሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጠለፋው እንደተፈፀመባት በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የመነሐሪያ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ፖሊስ አያይዞም፤ የተበዳይን ሁኔታ በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት በውል የሚታወቅ ባይሆንም ፖሊሳዊ ሥራዎችን በከፍተኛ ርብርብ እና ቅንጅት ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።

ተጠርጣሪው ተበዳይን ጠልፎ ከተሰወረ በኋላ ወደ ትውልድ መንደሩ እና ከሐዋሳ በቅርብ ርቀት ወደምትገኘው ሐገረ ሰላም ወደምትባል መንደር ይዟት መሄዱን ፖሊስ አስታውቋል።

ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ መረጃው እንደደረሰው ወደ አካባቢው በስውር ቢያቀናም ተጠርጣሪ መረጃው ቀድሞ ደርሶት ስለነበር ስፍራ እንደቀየረ ታውቋል።

ግለሰቡ የፖሊስን እንቅስቃሴ ቀድሞ መረጃው እንዲደርሰው የሚያደርጉ አካላት ከመኖራቸው ጋር ተዳምሮ የክትትል ሥራውን አስቸጋሪ ማድረጉንም ፖሊስ አስታውቋል። 

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *