ሁዋዌ ከግንቦት 16 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም በቻይና ሼንዘን ከተማ ባካሄደው የሁዋዌ አይሲቲ ዓለም አቀፍ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት ተማሪዎች የሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን አጠናቅቀው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
በውድድሩ ከ36 አገሮች የተውጣጡ 146 ቡድኖች የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ሶስት አባላት ያላቸው ሶስት ቡድን በመሆን በፕራክቲካል ትራክ (ዳታኮም፣ ሴኪዩሪቲ፣ WLAN፣ ቢግ ዳታ፣ ስቶሬጅ፣ AI፣ OpenEuler እና OpenGaussን ያካትታል) ሁለት ቡድን እና አንድ ቡድን በኢኖቬሽን ትራክ ተሳትፈዋል።
በኢኖቬሽን ትራክ የተወዳደሩት ተማሪዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሃሳብ ይዘው የቀረቡ ሲሆን ተማሪዎቹ “የግእዝ ፊደላት ክላሲፋየር” የተሰኘ መወዳደሪያ ይዘው ቀርበዋል፡፡
የሁዋዌ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ሊዩ ጂፋን ተማሪዎቹ ባመጡት ውጤት መደሰታቸውን ገልጸው ድርጅቱ የአይሲቲ ዘርፉን ለማጠናከርና ተተኪዎችን ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተማሪዎቹም በውጤታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ውድድሩ የሁዋዌን ዋና መስሪያ ቤት ከመጎብኘት አንስቶ አለምአቀፍ ተሞክሮ ያገኙበት በመሆኑም መደሰታቸውን ገልጸዋል፣
እነዚህ ተማሪዎች አገራቸውን ወክለው በዚህ ውድድር ለመሳተፍ የአገር ውስጥ ማጣሪያ ውድድሮችን በማለፍና በአገር አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮችም በማሸነፍ ነው።
ተማሪዎች የተገኙት ከጎንደር ፣ ዋቸሞ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ነው።