በአዲስ አበባ ለሰላማዊ ሰልፍ ወደ አደባባይ የወጡ ሁለት ሰዎች ህይወታቸው አለፈ

ፖሊስ በስፍራው በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሰው ሕይወት ማለፉን ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ አንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች መስጂዶች ፈርሰዋል በሚል ምክንያት በመርካቶ ዙሪያ በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

ፖሊስ ባወጣው መግለጫ በተፈጠረው ረብሻና ግርግር ህግ በማስከበር መደበኛ ሥራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱንም አስታውቋል።

በተለይም በተለምዶ ጋዝ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተፈጥሮ በነበረ ግርግር ሁለት ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ሆስፒታል ከተላኩ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል ተብሏል።

በተጨማሪም አራት ግለሰቦች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ህግን ለማስከበር በተሰማሩ 37 የፖሊስ አመራርና አባላት እንዲሁም 15 የሚሆኑ የተለያዩ የፖሊስ አጋዥ ሀይሎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና መላካቸውንም ገልጿል።

ረብሻውን ባስነሱት አካላት በተጨማሪ ንብረትነታቸው የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በሆኑ ሁለት አውቶቡሶች ላይ ጉዳት መድረሱንም በመግለጫው አመላክቷል።

መነሻውን አንዋር መስጂድ ያደረገው ረብሻ በጋዝ ተራ፣ ቆርቆሮ ተራ፣ ሰባተኛ አካባቢ፣ አመዴ እና በተለያዩ አካባቢ ለማዛመት የተሞከረ ቢሆንም በፀጥታ አካሉ ጥረት ረብሻው ሳይስፋፋ መቆጣጠር ተችሏልም ተብሏል።

ሰልፉን በመምራትና በማስተባበር ዋነኛ ተሳትፎ የነበራቸው 114 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ምክር ቤት በበኩሉ በሸገር ከተማ እየተፈጸሙ ያሉ የመጅድ ፈረሳዎችን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ላይ በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ የወሰደውን እርምጃ ተቃውሟል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ድርጊት ተቀባይነት የለውም ያለው ምክር ቤቱ ያልተመጣጠነ እና ህገወጥ እርምጃ በወሰዱ የጸጥታ ሀይሎች ላይ ህጋዊ ቅጣት እንዲጣልባቸውም ጠይቋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *