ኢትዮጵያ በሼንዘኑ ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ውድድር ላይ በዘጠኝ ተወዳዳሪዎች ትወከላለች

የቻይናዋ የቴክኖሎጂ ማዕከል ሼንዘን ከተማ ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ውድድርን ከግንቦት 16 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ታስተናግዳለች፡፡

በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ወደ ቻይና ያቀኑ ሲሆን ለተወዳዳሪዎቹ የአሸኛኘት ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

ውድድሩን ህዋዌ ያዘጋጀው ሲሆን በየሀገሩ በተካሄደ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ አሸናፊ የሆኑ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ተማሪዎቹ በዚህ  ዓለም አቅፍ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ያቀኑት የተለያዩ ሀገር አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳትፈው በየደረጃው በአሸናፊነት በማጠናቀቃቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያን በዚህ ውድድር ላይ የወከሉት ዘጠኙ ተማሪዎች  የተገኙት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ዋቸሞ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ነው።

በውድድሩ ተማሪዎቹ  እያንዳንዳቸው ሶስት አባላት ያላቸው ሶስት ቡድን ያላቸው ሲሆን በፕራክቲካል ትራክ (ዳታኮም፣ ሴኪዩሪቲ፣ WLAN፣ ቢግ ዳታ፣ ስቶሬጅ፣ AI፣ OpenEuler እና OpenGaussን ያካትታል) ሁለት ቡድን እና አንድ ቡድን በኢኖቬሽን ትራክ  ይሳተፋሉ።

በኢኖቬሽን ትራክ የሚወዳደሩት ተማሪዎች የራሳቸውን የፈጠራ ሃሳብ ይዘው የሚቀርቡ ሲሆን ተማሪዎቹ “የግእዝ ፊደላት ክላሲፋየር” የተሰኘ ውድድር ይዘው ቀርበዋል፡፡

ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ቻይና ላቀኑ ተማሪዎች በተዘጋጀ የሽኝት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለወጣት ተማሪዎች ዓለም አቀፍ ልምድ ማግኘት አነቃቂና አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

“ይህ እድል ያላችሁን ክህሎትና ተሰጥኦ የምታሳዩበትና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ጋር የምትገናኙበት ልዩ እድል ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ እንደጣራችሁና ከዚህም የተሻለ እንደምትሰሩ እምነቴ ነው፡፡” ብለዋል። አክለውም ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ስለወከላችሁ ልትኮሩና በማሸነፍም የዚህ ታላቅ ህዝብ ኩራት እንደምትሆኑ አምናለሁ ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዓለም በፍጥነት እያደጉ ካሉ ኢንዱስትሪዎች አንዱ እንደመሆኑ በዘርፉ የሰለጠኑ ብቂና በቁ ባለሙያዎች እንደሚሻ ገልጽው “ይህም ውድድር አቅማችሁን፣ ክህሎታችሁንና እውቀታችሁን የምታሳዩበት በመሆኑ በመተጋገዝና መደማምጥ በአሸናፊነት ልትወጡት ይገባል ብለዋል። በመጨረሻም ሁዋዌ ለተማሪዎቹ ለፈጠረው ዓለም አቅፍ እድልም በትምህርት ሚኒስቴር ስም አመስግነዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *