በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም ማዕከሉን በትግራይ ክልል አድርጎ ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት፣ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ በአገር ላይ መድረሱን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ አደረገ።
የገንዘብ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ተቋማቸው በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተካሄደው ጦርነት የደረሰውን ጉዳትና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት (Damage and Needs Assessment) ማከናወኑን ገልጸዋል ።
በጥናት ግኝቱ መሠረትም ያጋጠመው አጠቃላይ ጉዳትና የኢኮኖሚ ኪሳራ በአጠቃላይ 28 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን ተገልጿል።
ለምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተቀመጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ ‹‹22 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 20.4 በመቶ የሚገመት ጉዳት›› ደርሷል።
በዚሁ ምክንያት የደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ደግሞ፣ ‹‹ስድስት ቢሊዮን ዶላር ወይም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 5.5 በመቶ የሚገመት የኢኮኖሚ ኪሳራ (Economic Loss)›› መድረሱን ሪፖርቱ ያመለክታል።
ግጭትና ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ጠቅላላ ነዋሪዎች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በጦርነቱ በቀጥታ ተጎድተዋል ሲል ሪፖርተር ዘግቧል።
በዚህ ውስጥ ምክንያትም ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑት የአገሪቱ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት የከፋ ድህነት ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል።
ሚኒስትሩ ባቀረቡት ሪፖርት የተቀመጠው የጉዳት መጠን፣ ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት ከውጭ አበዳሪዎች ለኢኮኖሚ ልማት ተበድራ ካልመለሰችው አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ጋር እኩል ሆኗል።
በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብላል።