የመደ ወላቡ ዩንቨርሲቲ 20 መምህራን በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው አለፈ
መምህራኑን ይዞ ሲጓዝ በነበረው ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 20 ደርሷል።
ዛሬ ረፋድ የመደ ወላቡ መምህራንን ይዞ ሲጓዝ በነበረው ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ እስካሁን ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር 20 መድረሱን ዩንቨርሲቲው አስታውቋል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ዛሬ ማለዳ ለማስተማር ወደ ሻሸመኔ ካምፓስ በመጓዝ ላይ እያሉ የትራፊክ አደጋ ደርሶባቸዋል።
መምህራኑን የጫነው ተሸከርካሪው መንገድ ስቶ ወደ ገደል በመግባቱ በተፈጠረው በዚህ የትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል።
ከአደጋው በሕይወት የተረፉት ሌሎች ሰዎች በአደባ፣ ዶዶላ እና ሮቤ ሆስፒታሎች ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢብራሂም ከሊል ተናግረዋል።
መምህራኑ የርቀት እና የማታ ትምህርት ተማሪዎችን በሻሸመኔ ካምፓስ ለማስተማር ነበር ጉዞ የጀመሩት።
በኢትዮጵያ ያሉ ተሽከርካሪዎች ብዛት አንድ ሚሊዮን ቢሆንም በትራፊክ አደጋ ከፍተኛ ሞት ከሚመዘገብባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል ቀዳሚ ሀገር ናት።
በ2022 ዓመት ብቻ በኢትዮጵያ ከ20 ሺህ በላይ የመንገድ ላይ ትራፊክ አደጋዎች የደረሱ ሲሆ ከ6ሺህ በላይ ዜጎችን ደግሞ ገድሏል ተብሏል።