ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲዋን ከማለዘብ ወደ ማሳመን መቀየሩን ገለጸች

የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜኑ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት  የደረሱ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም “የማለዘብ ዲፕሎማሲ” ስትከተል መቆየቷን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።

በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ እና ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ስራዎች በመሰራታቸው ይደርሱ የነበሩ ጫናዎች መቀነሳቸውን ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከማለዘብ ዲፕሎማሲ ወደ ማሳመን ዲፕሎማሲ መመለሷን የተናገሩት አምባሳደር መለስ የተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል መሪዎቻቸውን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ላይ መሆናቸውን አክለዋል።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተማም ከኒዮርክ እና ጀኔቫ በመቀጠል ሶስተኛዋ የዓለማችን የዲፕሎማሲ ከተማ ይዞታዋ መመለሷን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥም የደቡብ አሜሪካ፣ አውሮፓ ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ እስያ እና አፍሪካ ከፍተኛ መሪዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ግንኙነቶቻቸውን የሚያሻሽሉ ውይይቶች እና ስምምነቶችን እየፈጸሙ እንደሆነም ተገልጿል።

በቅርቡም የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ህብረት የተመሰረተበት 60ኛ ዓመት በድምቀት እንደሚከበር ውና በዓሉን ለማድመቅ የሚሰራ ብሔራዊ ኮሚቴ መዋቀሩንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አንድ የአፍሪካ አንድነት መስራች እና አባል ሀገርነቷ በዓሉን በድምቀት እንደምታከብርም አምባሳደር መለስ ገልጸዋል ።

ይህ በዚህ እንዳለም ቃል አቀባዩ በሱዳን እየተካሄደ ስላለው ግጭት ዙሪያ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በሱዳን ግጭት ጉዳይ ከሱዳናዊያን ህዝብ ውጪ የትኛውንም ወገን እንደማትደግፍ አምባሳደር መለስ አክለዋል።

የሱዳን ግጭት ሊፈታ የሚችለው በራሳቸው በሱዳናዊያን የሚመራ የሰላም ውይይት እንጂ ከውጭ ሀገራት በሚመጣ መፍትሔ ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላትም ኢትዮጵያ ታምናለችም ተብሏል።

ይሁንና ኢትዮጵያ በኢጋድ እና በሌሎች አካላት የተጀመሩ ጥረቶችን እንደምትደግፍ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *