ፍሊንትስቶን ሪልስቴት 10 ሚሊዮን አክሲዮኖችን ለሽያጭ አቀረበ

ደርጅቱ በቀጣዮቹ አምስት አመታት ውስጥ 10 ሺህ ቤቶችን እንደሚገነባ አስታውቋል፡፡

ከ30 አመታት በላይ በመኖሪያ ቤት ግንባታ እና በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተሰማራዉ ፍሊንትስቶን ሪልስቴት 10 ሚሊዮን አክሲዮኖችን ለገበያ ማቅረቡን አስታዉቋል።

የፍሊንትስቶን መስራችና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጸደቀ ይሁኔ እንደተናገሩት ከ20 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 2 ሚሊዮን ብር ድረስ ዋጋ ያላቸዉን አክሲዮኖች ለሽያጭ መቅረባቸዉን ተናግረዋል። የአንዱ አክሲዮን ዋጋም 1 ሺህ ብር መሆኑን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ከሚቀጥለው ሐምሌ ጀምሮ ሽያጩ ይጀመራል የተባለ ሲሆን ባለ አክሲዮኖች ባላቸዉ የድርሻ መጠን ተሰልቶ አልያም በፍላጎታቸዉ ተጨማሪ ገንዘብ ከፍለዉ የቤት ባለቤት መሆን የሚችሉበት እድል መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡

በዋነኛነት አክሲዮን ሽያጩ ያስፈለገዉ ተጨማሪ ካፒታል ለማግኘት ፣ ድርጅቱን ከ አምስት ሰዎች የሽርክና ባለቤትነት ወደ ህዝብ ንብረት ለመለወጥ መሆኑ በመድረኩ ተነስቷል።

በተጨማሪም በቀጣዮቹ አምስት አመታት ድርጅቱ 10 ሺህ ቤቶችን ገንብቶ ለደንበኞቹ ለማቅረብ አቅጃለሁ ያለ ሲሆን ለዚህም የአክሲዮን ሽያጩ ትልቅ አቅም እንደሚጨምርለት ተገልጿል።

ባለ አክሲዮኖች በድርጅቱ ጥርጣሬ ከገባቸዉ 10 በመቶ አባላቱ ተሰባስበዉ ጠቅላላ ጉባኤ ማስጠራት የሚችሉበትን እድል ይሰጣል የተባለ ሲሆን ለዚህም ተቋሙ የራሱን የሞባይል መተግበሪያ በማበልጸግ ላይ መሆኑን ኢንጅነር ጸደቀ ተናግረዋል።

ተቋሙ በአክሲዮን ባለቤትነት መያዙ ፤ በመንግስትም ሆነ በግል ዘርፉ እየተገነቡ ላሉ እና ብዙ ድክመቶች ከሚታይባቸዉ ፕሮጀክቶች የመፍትሔ ሀሳብ የሚሰጥ መሆኑ ታምኖበታል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *