ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ አቅዳ እንደነበር ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርቱ ላይ እንደገለጸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ወደ አገር ውስጥ ለመሳብ ታቅዶ 2.67 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
የኮሚሽኑ አፈጻጸም የዕቅዱን 61 በመቶ ብቻ ያሳካ ሲሆን በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት፣ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያለው አለመረጋጋት እንዲሁም በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ምክንያት ያጋጠመው የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ለአፈጻጸሙ መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶች መካከል አብዛኞቹ የግብርና፣ የአምራች፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽንና፣ የቱሪዝምና የጤና ዘርፎች ናቸው፡፡
ወደ አገር ውስጥ ከገቡት ኢንቨስተሮች መካከልም ቻይና፣ ህንድና ኬንያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ ተብሏል፡፡
ከኢንዱስትሪ ፓርኮች በዘጠኝ ወራት 118 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች ወደ ውጭ ሀገራት የተላኩ ሲሆን ለ55 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ የምርት ዘርፎች የተሰማሩ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ከመንግስት ተቋማት መሪዎች እና ባለሙያዎች በሚጠየቁ ክፍያ ምክንያት መማረራቸው ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንት ኮሚሽኑንን ሪፖርት በገመገመበት ወቅት እንደገለጸው በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ ኩባንያዎች ቅሬታ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በዚህ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባደረጉት ምልከታ ኢንቨስተሮች የሚጠይቋቸውን ከትንሽ እስከ ትልቅ አገልግሎቶች በገንዘብ እየገዙ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በፓርኩ ላይ የባለቤትነት ስሜት ባለመኖሩ ፓርኮች ውስጥ እየገቡ ዘረፋ እየተፈጸባቸው መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት በመስክ ምልከታቸው ወቅት መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በኢስተርን ኢንዱስትሪ ፓርክ በተሰማሩ ኢንቨስተሮች ላይ በሚፈጸም የስርቆት፣ ሙስና እና ቢሮክራሲ ምክንያት የተማረሩ 51 ባለሀብቶች ለቀው መሄዳቸው ተገልጿል፡፡