አቶ ልደቱ አያሌው እጃቸውን ለመስጠት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ገለጹ

ፖለቲከኛው ልደቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት በሽብርተኝነት ለቀረበባቸው ክስ በአደባባይ ለመሟገት እንደሆነ ተናግረዋል

መንግስት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማናጋት ሙከራ አድርገዋል በሚል በሽብርተኛነት ከወነጀላቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ልደቱ የተከሰሱበትን ክስ በአደባባይ ለመሞገት መወሰናቸው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ጽፈዋል፡፡

በፅሁፋቸውም “ከአገዛዙ አፈና ፣ እስርና ግድያ ሸሽቶ በማምለጥ የሚመጣ መፍትሄ የለም። ትግላችን ሰላማዊና ህጋዊ እስከሆነ ድረስ በገፍ እየታሰርንና እየሞትን አገዛዙ በሀይልና በአፈና ሊያሸንፈን እንደማይችል ተስፋ ልናስቆርጠው ይገባል። በዚህ መጠን ዋጋ ለመክፈል ካልቆረጥን በስተቀር የአገርና የህዝብ ህልውና ከጥፋት ሊድን አይችልምና።” ያሉ ሲሆን “ይህንን በለጋ የልጅነት ዘመኔ ለራሴ የገባሁትን የትግል ቃል-ኪዳንና የምታመንለትን የሰላማዊነትና ህጋዊነት መርህ መሰረት በማድረግ ወደ አገሬ ለመመለስና የዶ/ር ዐቢይን የፈጠራ የአሸባሪነት ክስ እንደተለመደው በፍትህ አደባባይ ለመጋፈጥ ወስኛለሁ።” ማለታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ አስታውቀዋል፡፡

“ስለሆነም በታሰርኩ ቁጥር ከእኔ በላይ ስቃዬን የምትሰቃዩ ቤተ-ዘመዶቸ፣ ጓደኞቸ፣ የሃሳብ ደጋፊዎቸና የትግል አጋሮቸ ይህንን ውሳኔዬን የሞኝነት፣ የአጉል ጀብደኝነት ወይም የመንግስትን የጭካኔ ደረጃ በአግባቡ ያለመረዳት ድክመት አድርጋችሁ እንዳታዩብኝና ያልተገባ ጫና እንዳትፈጥሩብኝ በዚህ አጋጣሚ በአክብሮት እማፀናለሁ። ይህንን ውሳኔ በሚገባ አስቤበትና ከልቤ አምኘበት የወሰንኩት ስለሆነ በሞራል ልታግዙኝ ይገባል እንጂ ልታዝኑልኝም ሆነ ልታዝኑብኝ አይገባም እላለሁ። ” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታክ አይረሴ በሚባለው ምርጫ 97 ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ የሆኑት አቶ ልደቱ ከኢህአዴግ እስከ ብልጽግና መራሽ መንግስት በሽብርተኝነት በመከሰስ ላይ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት በካቢኔ አባልነት እንዲካተቱ ግብዣ ቀርቦልኝ ነበር የሚሉት አቶ ልደቱ በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት በመቃወም ቀዳሚው ፖለቲከኛም ነበሩ፡፡

የፌደራል መንግስት እና ህወሃት መካከል የተጀመረው ጦርነት የሀይል የበላይነትን ለመቆጣጠር የሚደረግ ነው፣ ጦርነቱ አማራን አይጠቅምም እና ሌሎችንም ሀሳቦች ሲሰነዝሩም ነበር፡፡

ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ እየተንቃቀሱ ነው በሚል ከሌሎች ሰዎች ጋር ክስ የቀረበባቸው አቶ ልደቱ አያሌው ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እጃቸውን ሰጥተው በፍርድ ቤት እንደሚከራከሩ ገልጸዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *