የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሹልዝ አዲስ አበባ ገቡ

የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሹልዝ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል።

መራሄ መንግሥቱ የጀርመን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ፣ ባለሀብቶችን፣ የተቋማት መሪዎችን እንዲሁም በርከት ያለ የልዑካን አባላትን አስከትለው ነው ቦሌ አየር ማረፊያ የደረሱት።

ሹልዝ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የመራሄ መንግሥቱን የሥራ ጉብኝት አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት መግለጫ፤ ጉብኝቱ ታሪካዊና ጠንካራ የኹለትዮሽ ግንኙነት ላላቸው ኢትዮጵያና ጀርመን ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ትብብሮችን ለማሳደግ ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማላቅ  የመራሄ መንግሥት ሹልዝ ጉብኝት ትርጉም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በኢትዮጽያ ቆይታቸው ከፕሬዘዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ እና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በቆይታቸውም ስለሰብዓዊ እርዳታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኹለትዮሽ ትብብር እንዲሁም እንደሱዳን ግጭት ያሉ ቀጠናዊ ችግሮችን መፍታት ላይ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡

የኦላፍ ሹልዝ ጉዞ ስልጣን ከያዙ በኋላ ወደ አፍሪካ የሚደረግ ኹለተኛ ጉዟቸው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ኬንያ ያቀናሉ ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *